Addis Standard Amharic
17.9K subscribers
4.87K photos
123 videos
3 files
3.87K links
አዲስ ስታንዳርድ በጃኬን አሳታሚ ኃ.የተ.የግ.ማ. ባለቤትነት ስር የሚታተም በኢትዮጵያ የሚገኝ ነፃ እና ገለልተኛ ሚዲያ ነው። አዲስ ስታንዳርድ አማርኛ የአዲስ ስታንዳርድ እንግሊዝኛ ሕትመት አካል ነው።
ፌስቡክ: https://rb.gy/xwxb3
ትዊተር (X)፡ https://rb.gy/34uh4
Download Telegram
ዜና፡ የ #ትግራይና #አፋር ሕዝቦችን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ የሰላም ኮንፈረንስ በአዲ-ጉደም ከተማ ተካሄደ

በትግራይ እና በአፋር ሕዝቦች መካከል ያለውን አንድነት እና አብሮነት ለማጠናከር ያለመ የሰላም ኮንፈረንስ በትግራይ ክልል በአዲ-ጉደም ከተማ ተካሄደ። በኮንፈረንሱ ላይ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

እንደ ትግራይ ክልል መገናኛ ብዙኃን ዘገባ፣ ኮንፈረንሱ ትኩረቱን ያደረገው በትግራይ ክልል ሕንጣሎ ወረዳ በሚገኘው አራ-ዓለም ሰገዳ እና በአፋር ክልል አባዓላ ወረዳ ጋሌሶን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪዎች መካከል ሰላማዊ ግንኙነትን መፍጠር ላይ ነው ተብሏል። ይህም የሕዝብ ለሕዝብ ትብብር ለዘላቂ ሰላም መሠረት መሆኑ ተመልክቷል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ምስራቅ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ከላሊ ሐጋዚ፣ በትግራይና በአፋር ሕዝቦች መካከል ያለውን አንድነት አስፈላጊነት ገልጸው በሁሉም ዘርፎች ትብብር እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

“ባለሥልጣናት ይመጣሉ ይሄዳሉ፤ ጎረቤትና ማኅበረሰብ ግን ዘላቂ ናቸው” ያሉት አስተዳዳሪው፣ ሰላምን ለማደፍረስ የሚጥሩ አካላትን በጋራ መመከት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሕንጣሎ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጎይቶም ተስፋዬ በበኩላቸው፣ ሁለቱ ማኅበረሰቦች በታሪክ በሰላም ሲኖሩ የቆዩ መሆናቸውንና አለመግባባቶችን በሽማግሌዎችና በጎረቤቶች አማካኝነት በውይይት እንደሚፈቱ ገልጸዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ፡ https://addisstandard.com/Amharic/?p=10496
የገንዘብ ሚኒስትሩ የአለም ባንክ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠየቁ፤ ከባንኩ ከፍተኛ አመራር ጋርም በኢኮኖሚ ማሻሻያው ዙሪያ መክረዋል

ኢትዮጵያ የጀመረችውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ከዳር ለማድረስ፣ ከዓለም ባንክ የሚደረገላት የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቋን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ውይይቱ የተካሄደው ትናንት ጥር 18/2018 ዓ.ም በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እና በዓለም ባንክ ማኔጂንግ ዳይሬክተር እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዌንካይ ዣንግ መካከል ነው።

በውይይታቸውም የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ መንግሥት እያከናወነ ስላለው የማሻሻያ ፕሮግራም ለዣንግ ገለጻ አድርገዋል። የዚህ ማሻሻያ ዋና ዓላማ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በግል ዘርፉ ወደሚመራ የኢኮኖሚ ሥርዓት ማሸጋገር እንደሆነም አስረድተዋል።

ሚኒስትሩ በተጨማሪም የኢኮኖሚ ዕድገት ምንጮችን ለማስፋት፣ የዲጂታል ኢኮኖሚ እና የቱሪዝም ዘርፎችን ለማነቃቃት፣ እንዲሁም በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሚደረግ የተሻለ ትስስር ቀጣናዊ ውህደትን ለማጠናከር የታቀዱ ዕቅዶች ላይ ገለፃ አድርገዋል።

አቶ አህመድ ሽዴ፣ የዓለም ባንክ በዋና ዋና የልማት ዘርፎች ላይ ለሚያደርገው "ከፍተኛ ድጋፍ" ያላቸውን አድናቆት መግለጻቸውን ሚኒስቴሩ በሰጠው መግለጫ ጠቅሷል። አክለውም ባንኩ የኢትዮጵያን የማሻሻያ ሥራዎች እና ለልማት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ተግባራት በማስቀጠል ረገድ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ተጨማሪ ለማንበብ:- https://www.facebook.com/share/1CLXCv6zRA/
#አሜሪካ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የአሜሪካ አፍሪካ ዕዝ አዛዥ በኢትዮጵያ አየር ኃይል የተዘጋጀውን ዓለም አቀፍ የአቭዬሽን ኤክስፖ ጎበኙ

የአሜሪካ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክርስቶፎር ላንዳው እና የአሜሪካ አፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አንደርሰን በኢትዮጵያ አየር ኃይል የተዘጋጀውን ዓለም አቀፍ የአቭዬሽን ኤክስፖ መጎብኘታቸውን መከላከያ ሠራዊት አስታወቀ።

በኢትዮጵያ በኩል የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በጉብኝቱ መሳተፋቸውም ተገልጿል።

በዚህ ኤክስፖ አየር ኃይልን ጨምሮ የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ግሩፕ ፣መከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ፣ የመከላከያ ዩኒቨርስቲ እና ሌሎችም አለም አቀፍ ደርጅቶች ምርቶቻቸውን ለዕይታ አቅርበዋል ተብሏል።

በኤክስፖው የቀረቡት ወታደራዊ ቴክኖሎጂ ውጤቶች የኢትዮጵያን የረጅም ዘመን ስኬት የሚያሳዩ ስለመሆናቸው መከላከያ ሠራዊት መረጃ አመላክቷል።

የአሜሪካ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክርስቶፎር ላንዳው ከጉብኝቱ በኋላ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀበባል ምስጋና አቅርበው፤ ኢትዮጵያ በመገኘታቸው ክብር እንደሚሠማቸው ገልፀዋል። በኢትዮጵያ እና አሜሪካ መካከል ያለው ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጠልም ተናግረዋል።

የአሜሪካ አፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አንደርሰን በበኩላቸው ለቀጠናው ሰላም በተለይም እንደ አልሸባብ እና አይኤስኤስ ያሉ ሽብረተኞችን ለመከላከል እና ለመደምሰስ በጋራ እንሰራለን ማለታቸውን መከላከያ ሠራዊት አስታውቋል።
የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ በሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ዝውውር እና በሰው መነገድ ወንጀል በተሳተፉ 28 ተከሳሾች ላይ ክስ መሰረተ

የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ 1 ሺህ 8 መቶ የሚሆኑ ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ በማዘዋወር፣ በከባድ የሰው ልጅ መነገድ እና በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀል በተሳተፉ 28 ተከሳሾች ላይ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ክስ መመስረቱን ፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ተከሳሾቹ የተደራጀ የወንጀል ቡድን በመመስረት ሰዎችን በሊቢያ በኩል ወደ አውሮፓ ለማሻገር በማታለል እጅግ አሰቃቂ ለሆነ እንግልት እና ዝርፊያ ዳርገዋል ተብሏል።

የዐቃቤ ሕግ ክስ፣ ተከሳሾቹ በስራቸው ሌሎች ደላሎችን በመመልመል ሰዎችን የተሻለ ኑሮ እንደሚያገኙ በማሳመን ወደ ባህርዳር እና ጎንደር በመላክ በኩል ወደ ሱዳን ድንበር በሕገ-ወጥ መንገድ ሲያወጡ መቆየታቸውን ያመለክታል።

ተጎጂዎቹ የኢትዮጵያን ድንበር ካለፉ በኋላ በሊቢያ በሚገኙ መጋዘኖች ውስጥ እንዲታጎሩ በማድረግ፣ በሕይወት ለመቆየት ብቻ የሚበቃ ምግብ እየተሰጣቸው ለቤተሰቦቻቸው በመደወል ከፍተኛ ገንዘብ ሲጠየቅባቸው እንደነበር ተገልጿል።

ገንዘብ በፍጥነት መክፈል ያልቻሉ ተጎጂዎች እጅግ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ እየተደበደቡና እየተሰቃዩ ምስላቸው በቪዲዮ ተቀርጾ ወደ ቤተሰቦቻቸው በመላክ ከፍተኛ ጫና ይደረግባቸው እንደነበር ክሱ ያሳያል።

በዚህ የወንጀል ሰንሰለት ውስጥ በሕግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ስምንት ተከሳሾች ብቻ በባንክ ሂሳባቸው ከሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰባቸው መረጋገጡን የዐቃቤ ህግ ክስ ተመላክቷል።

https://web.facebook.com/AddisstandardAmh/posts/pfbid02nkdyiZa84kQ3YrMt29gntKtF5aBQskWZECkFbipqt9cYFNf7zW4sgwe1fLbbsUppl
#ኢትዮጵያና #አሜሪካ ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በጋራ ለመስራት መስማማታቸው ተገለፀ

የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በዛሬው ዕለት የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አርኤም አንደርሰንን በቢሯቸው ተቀብለው ካነጋገሩ በኋላ የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ኢንጂነር አይሻ በዚሁ ወቅት ሁለቱ ሀገራት ከዚህ በፊት የቆየ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ አሁን ላይ እያደገ የመጣውን ከፍተኛ የዲፕሎማሲና ወታደራዊ ግንኙነት ወደላቀ ስታራቴጂካዊ የሥራ አጋርነት በማሳደግ የሁለቱን ሀገራት እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መስማማታቸውን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በሰላምና በፀጥታ ጉዳዮች በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ መድረሳቸውን ገልፀው፤ የሁለቱንም ሀገራት ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እና ሽብርተኝነትን በጋራ ለመዋጋት ከስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አርኤም አንደርሰን በበኩላቸው የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን ለማክበር ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ታሪክን ለማሰላሰልና የወደፊት ትብብርን ለማጠናከር ትርጉም ያለው አጋጣሚ እንደሆነ ገልፀዋል።

አክለውም የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው በኢትዮጵያ አየር ኃይል አከባበር ላይ ለመገኘትና ለመሳተፍ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት እንደገና ለማየትም ዕድል እንደሰጣቸው በመግለጫቸው ላይ ጠቁመዋል፡፡

በተለይም የጋራ ቀጠናዊ የደህንነት ተግዳሮቶችን ለመፍታትና የአጋርነት ዕድሎችን ለመጠቀም እንዲሁም የሁለቱን አገሮች ግንኙነት እንደገና ለማጠናከር ትልቅ አጋጣሚ መፍጠሩን መናገራቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ተጨማሪ ለማንበብ: https://www.facebook.com/share/1C1JPYK1q3/
ዜና: በኢትዮጵያ በወርቅ ማልማት ተግባር የተሰማራው የካናዳው አላይድ ጎልድ በ4 ቢሊዮን ዶላር ለቻይናው ዚጂን ጎልድ ሊሸጥ ነው

በኢትዮጵያ ውስጥ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በማንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው የካናዳው የወርቅ ማዕድን ኩባንያ አላይድ ጎልድ በቻይናው ዚጂን ጎልድ ኢንተርናሽናል መገዛቱን ፋይናንሺያል ታይምስ ዘግቧል። ግዥው በሙሉ በጥሬ ገንዘብ የሚፈጸም ሲሆን፣ ዋጋውም በግምት 4 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነው ተብሏል።

በሆንግ ኮንግ የአክሲዮን ገበያ የተመዘገበው ዚጂን ጎልድ ኢንተርናሽናል፣ አላይድ ጎልድን በ5.5 ቢሊዮን የካናዳ ዶላር (4 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር) ለመግዛት ተስማምቷል። ፋይናንሺያል ታይምስ እንደዘገበው፣ ይህ ግዢ ሊፈጸም የቻለው የወርቅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ተከትሎ፣ በማዕድን ዘርፉ ውስጥ ያሉ ኩባንያዎች እርስ በርስ በመጣመር አቅማቸውን እያጠናከሩ በመሆናቸው ነው።

አላይድ ጎልድ በኢትዮጵያ፣ በማሊ እና በኮትዲቩዋር የማዕድን ማውጣት ሥራዎች አሉት። ኩባንያው በስምምነቱ መደሰቱን የገለጸ ሲሆን፣ በዚህ ግዢ የአንድ አክሲዮን ዋጋ 44 የካናዳ ዶላር እንዲሆን ተደርጓል። ይህም ስምምነቱ ከመታወቁ በፊት ከነበረው የ30 ቀናት አማካይ የአክሲዮን ዋጋ ጋር ሲነጻጸር የ27 በመቶ ጭማሪ አለው ተብሏል።

ይህ የዋጋ መናር የወርቅ ዋጋ በዓለም ገበያ በመጨመሩ ምክንያት ባለሀብቶች በማዕድን ሀብቶች ላይ ያላቸው ከፍተኛ ፍላጎት ማደጉን ያሳያል።

ተጨማሪ ለማንበብ:- https://www.facebook.com/share/1FBCWxygmK/
#ዘመን_ባንክ አጠቃላይ ሀብቱ 106 ቢሊዮን ብር መድረሱን ገለፀ

ዘመን ባንክ በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ውስጥ አጠቃላይ ሀብቱን 106 ቢሊዮን ብር ማድረሱን የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደረጀ ዘበነ አስታወቁ።

ባንኩ በዚሁ የመንፈቀ ዓመት ጊዜ ውስጥ የደንበኞች ተቀማጭ ገንዘብ 80 ቢሊዮን ብር መድረሱን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ ይህም ባንኩ የተረጋጋ ዕድገትና ጠንካራ የደንበኞች አመኔታ እንዳለው የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጥር 16 ቀን 2018 ዓ.ም በተካሄደው የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ላይ እንደተገለፀው፣ ባንኩ በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን፣ የተከፈለ ካፒታሉንም ወደ 14 ቢሊዮን ብር አሳድጓል።

አቶ ደረጀ አፈፃፀሙን ሲያብራሩ “ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲወዳደር የዘንድሮው የላቀና ስኬታማ የሥራ ጊዜ ያሳለፍንበት ነበር” ብለዋል።

የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ እንዬ ቢምር በበኩላቸው፣ ለተመዘገበው ውጤት ለአመራሩና ለሠራተኞች ምስጋና አቅርበው፤ ቦርዱ በሁለተኛው ግማሽ ዓመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ አሳስቧል።

የባንኩ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በተገኙበት በዚህ ውይይት ላይ፣ የተመዘገበው ስኬት የባንኩን ደንበኛ ተኮር አገልግሎትና ጥንቃቄ የተሞላበት የፋይናንስ አስተዳደር የሚያረጋግጥ መሆኑ ተገልጿል።
ዜና፡ ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ ከ3,400 በላይ #ኢትዮጵያውያን#ሳዑዲ–ዓረቢያ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ

ባለፈው አንድ ሳምንት ውስጥ 3,422 ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ዓረቢያ ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ይህም ከመስከረም 2018 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሀገር የተመለሱ ዜጎችን ቁጥር 45,093 አድርሶታል።

ሚኒስቴሩ በዚህ ሳምንት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ተመላሾቹ በ14 መደበኛ በረራዎች የገቡ ሲሆን፣ ስብጥራቸውም 3,337 ወንዶች፣ 82 ሴቶች እና ሦስት ሕፃናትን ያካተተ ነው። ከእነዚህም መካከል 72 የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች መሆናቸው የተመለከተ ሲሆን፣ ይህም የተመላሾችን ተጋላጭነት እንደሚያሳይ ተገልጿል።

ይህ መጠነ ሰፊ ዜጎችን የመመለስ ዘመቻ በሳዑዲ ዓረቢያ በከባድ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ 70,000 ዜጎችን ለመመለስ በመጋቢት 2016 ዓ.ም የተጀመረው መርሃ-ግብር አካል መሆኑ ተገልጿል።

ይህ መርሃ-ግብር እንዲጀመር ምክንያት የሆነው በሳዑዲ ዓረቢያ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የሚፈጸሙ አሰቃቂ በደሎች ሪፖርቶች እየጨመሩ በመምጣታቸው ነው። ሂዩማን ራይትስ ዎች በነሐሴ 2015 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት፣ ከየካቲት 2014 ዓ.ም እስከ ሰኔ 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች በሳዑዲ ኃይሎች መገደላቸውን አስፍሯል።

https://addisstandard.com/Amharic/?p=10501
#ጣሊያን ሁለተኛውን የጣሊያን-አፍሪካ ጉባኤ የፊታችን የካቲት 6 በ #አዲስ_አበባ ታካሂዳለች

ጣሊያን ሁለተኛውን የጣሊያን-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ፣ በመጪው የካቲት 6/2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደምታካሂድ የሀገሪቱ መንግሥት አስታወቀ።

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጃ ሜሎኒ በዓመቱ የመጀመሪያ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ እንዳስታወቁት፤ ሁለተኛው የጣሊያን-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ምድር በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በዓመቱ የመጀመሪያ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ እንዳስታወቁት፤ ጉባኤው ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ምድር የሚካሄድ ሲሆን፣ ከአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን በሕብረቱ መንግሥታትና የሀገራት መሪዎች ጉባኤ ዋዜማ ላይ ይከናወናል።

የጉባኤው ፕሮግራም አካል በመሆን፣ በክብር እንግድነት ይገኛሉ ተብለው የሚጠበቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ሜሎኒ፣ የካቲት 7 ጠዋት በሚካሄደው የአፍሪካ ሕብረት መደበኛ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደርጋሉ ተብሏል።

የጉባኤው ዓላማ ጣሊያን ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ማጠናከርና እ.ኤ.አ. በጥር 2024 በሮም ይፋ የተደረገውን የ "ማቴ እቅድ" (Mattei Plan) ግቦች ማሳካት መሆኑን መግለጫው ጠቁሟል።

ዕቅዱ በጣሊያን እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ሥርዓት ያለው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አጋርነትን ለማሳደግ ያለመ ነው።

ጉባኤው በ "ማቴ ዕቅድ" ዋና ዋና ዓላማዎች ላይ በመመሥረት እንደ ዘላቂ ልማት፣ መሠረተ ልማት፣ ኢነርጂ፣ ትምህርትና ሥልጠና፣ ጤና ጥበቃ እና ግብርና ባሉ ዘርፎች ላይ ትብብርን በማሳደግ ላይ እንደሚያተኩር የጣሊያን መንግሥት ገልጿል።

ተጨማሪ ለማንበብ:- https://www.facebook.com/share/14WRuHoREp2/
ዜና፡ ምርጫ ቦርድ ለስምንት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ቅሬታ በሰጠው ምላሽ የዲጂታል ምዝገባው “ቴክኒካዊ እንጂ ፖለቲካዊ” ተፅዕኖ እንደሌለው ገለጸ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስምንት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ፣ የቀረቡት ቅሬታዎች “ሕጉንና አሠራሩን ካለመረዳት የመነጩ” ናቸው ሲል ዝርዝር ማብራሪያ ሰጠ።

ስምንት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትላንት ጥር 15 ቀን 2018 ዓም ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ገና በዕጩዎች ምዝገባ ጅምሮ ላይ ሳለ "ሰላማዊውን የፖለቲካ ምህዳር የሚያጨልሙ ተግዳሮቶች" እያጋጠሟቸዉ እንደሚገኝ አስታውቀው፣ ምርጫው "አሳታፊ፣ ሐቀኛ እና ተዓማኒ ሊሆን እንደማይችል" ማሳሰባቸው ይታወሳል።

ፓርቲዎቹ እንደሚሉት፣ ቦርዱ የዲጂታል ቴክኖሎጂ የምዝገባ ሥርዓት በቴክኒክ ደረጃ የመፈተሽ ዕድል አልተሰጣቸውም። በተጨማሪም በምዝገባ ወቅት እንደ መስፈርት የቀረቡት የልደት ምስክር ወረቀት እና የዓይን እማኝ ማቅረብ፣ በተለይ ከከተማ ውጭ ባሉ አካባቢዎች ፈጽሞ የማይታሰቡ እና ተቃዋሚዎችን ከፉክክር ሜዳው ለማውጣት የታቀዱ “የፖለቲካ ሴራዎች” ናቸው ብለዋል።

ቦርዱ ባወጣው መግለጫ፣ የዲጂታል የምዝገባ ሥርዓቱ ከሚያዝያ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሲቪል ማኅበራት ጋር በተደረገ ምክክር የበለጸገ መሆኑን ገልጿል። በዲጂታል የዕጩዎች ምዝገባ ሂደት ላይ የቀረቡትን ተግዳሮቶች አስመልክቶ፣ ሥርዓቱ ፓርቲዎችን ከውጫዊ ተፅዕኖ ነፃ ለማድረግና አሠራሩን ለማዘመን የተዘረጋ መሆኑን አስታውቋል።

https://addisstandard.com/amharic-election2026/?p=1216
#ሱዳን ጦር ከኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ የምትገኘውን #አል_ሲሊክ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይል ተዋጊዎች ማስለቀቁን አስታወቀ

የሱዳን ጦር ሀይል (SAF) ከኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ በብሉ ናይል ግዛት የሚገኘውን አል-ሲሊክ የተባለ ስትራቴጂካዊ ስፍራን፣ ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (RSF) ነፃ ማውጣቱን አስታወቀ።

አናዶሉ የዜና ወኪል ቅዳሜና እሁድ የተካሄደውን ከባድ ውጊያ ተከትሎ የሱዳን ጦር 4ኛ ክፍለ ጦር ሰኞ ዕለት ያወጣውን መግለጫ ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ፣ አካባቢውን “በታቀደ ወታደራዊ ኦፕሬሽን” መቆጣጠሩንና በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ተዋጊዎች ላይ ከፍተኛ የሰውና የንብረት ጉዳት ማድረሱን አስታውቋል።

ክፍለ ጦሩ አክሎም፣ በውጊያው ወቅት በአብዱልአዚዝ አል-ሂሉ የሚመራው የሱዳን ሕዝባዊ ነፃነት ንቅናቄ-ሰሜን (SPLM-N) ተዋጊዎችም መመታታቸውን ገልጿል።

እስካሁን ድረስ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ወይም ከሱዳን ሕዝባዊ ነፃነት ንቅናቄ-ሰሜን ወገን የተሰጠ መግለጫ የለም።

ይህ ወታደራዊ እንቅስቃሴ የተሰማው፣ ባለፈው እሁድ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እና የሱዳን ሕዝባዊ ነፃነት ንቅናቄ-ሰሜን ኃይሎች ከደቡብ ሱዳን ግዛት በመነሳት በብሉ ናይል አካባቢ በሚገኙ አል-ሲሊክ እና ሚልካን ላይ ሰፊ ጥቃት መክፈታቸውን መዘገቡን ተከትሎ ነው።

የሱዳን ባለሥልጣናት ጥቃቱን "የውጭ ወረራ" ሲሉ የገለጹት ሲሆን፣ ደቡብ ሱዳን ግዛቷ ለአጥቂዎቹ ማሰልጠኛ እና ወታደራዊ መሣሪያ ማስተላለፊያ እንዲሆን ፈቅዳለች ሲሉ ከሰዋል።

ተጨማሪ ለማንበብ:- https://www.facebook.com/share/14UTjiPhzrv/
ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ከ #አሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክሪስቶፈር ላንዳው እና ከአሜሪካ አፍሪካ እዝ አዛዥ ጄነራል ዳግቪን አንደርሰን ጋር ተወያዩ

ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ከአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክሪስቶፈር ቲ ላንዳው እና የአሜሪካ አፍሪካ እዝ አዛዥ ጄነራል ዳግቪን አንደርሰን ጋር በጽሕፈት ቤታቸው መወያየታቸውን አስታወቁ።

ዐቢይ አህመድ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸውን ባሰፈሩት መልዕክት “በጽሕፈት ቤታችን ከተገኙት ቲ ላንዳው እና ከጄነራል ዳግቪን አንደርሰን ጋር ተወያይተናል” ብለዋል። አክለውም ቀጣይነት ያለው ትብብር እና መከባበርን አፅንዖት ለሰጠው ደማቅ እና ገንቢ ውይይታችን ምስጋናዬን አቀርባለሁ ሲሉ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ክሪስቶፈር ላንዳውን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይታቸውም በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለውን የቆየ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ መምከራቸውን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡ ሁለቱ ወገኖች የጋራ ፍላጎት ባላቸው ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሐሳብ ልውውጥ አድርገዋል ተብሏል።

https://web.facebook.com/AddisstandardAmh/posts/pfbid0vbHHEj5A8xAYBx8vJA6a9njtNFJ9X8PrScmghCuSoajGR1G9muhTza8JZ34EbrEpl
#አማራ_ክልል የቢሊዮኖች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱ ቢገለጽም፤ የጸጥታው ሁኔታ ግን ግዙፍ ኩባንያዎችን ከክልሉ እያወጣ ነው

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ውስጥ ለ1,867 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፣ ባለፉት ስድስት ወራት 182.77 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች ፈቃድ ተሰጥቷል ብለዋል።

ለአምራች ኢንዱስትሪ፣ ለግብርና እና ለአገልግሎት ዘርፎች የሚውል 3,626.27 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን የጠቀሱት ኃላፊው፣ ይህም የክልሉን የኢንቨስትመንት ፍሰት በየጊዜው እየተሻሻለ መምጣቱን የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸዋል።

እንደ ቢሮው ኃላፊ ገለጻ፣ እነዚህ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ሲገቡ ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር የክልሉን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት "ትልቅ ሚና" እንደሚኖራቸው አመላክተዋል።

ይሁን እንጂ ይህ በንዲህ እንዳለ በክልሉ ባለው የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት ግዙፉ የጀርመን ሆርቲካልቸር ኩባንያ ሴሌክታ ዋን (Selecta One) ሥራውን አቁሞ ወደ ጎረቤት ሀገራት መዛወሩን ግንቦት 26 ቀን 2017 ዓ.ም ማስታወቁ ይታወሳል።

መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም አዲስ ስታንዳርድ እንደዘገበው፣ በምዕራብ ጎጃም ዞን ኩንዝላ አካባቢ ለዓመታት ሲንቀሳቀስ የነበረው ‘ሴሌክታ ዋን’ በክልሉ ባለው ግጭት ሳቢያ የሠራተኞቹን ደህንነት ማረጋገጥ ባለመቻሉ የምርት ጣቢያውን ወደ ኬንያ እና ዩጋንዳ ማዛወሩን አስታውቋል።

https://www.facebook.com/share/p/1ayKX9fAqK/
#ሆላንድ ፍርድ ቤት በአንድ #ኤርትራዊ የሰዎች አዘዋዋሪ ላይ የ20 ዓመት እስራት ፈረደ

የኔዘርላንድ ፍርድ ቤት ማክሰኞ ዕለት ስደተኞች የሚሰቃዩበትንና ቤተሰቦቻቸው የሚበዘበዙበትን የሰዎች ዝውውር ወንጀል ሲመራ በነበረ አንድ ኤርትራዊ ግለሰብ ላይ የ20 ዓመት እስራት ፈረደ።

ፍርድ ቤቱ አማኑኤል ወሊድ የተባለው ግለሰብ፣ ስደተኞችን ከኤርትራ በሊቢያ በኩል ወደ አውሮፓ በሚያጓጉዝበት ወቅት "ሰብአዊነት በጎደለው መልኩ" ይይዛቸው እንደነበር ገልጿል።

የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ ረኔ ሜላርድ ለአማኑኤል ወሊድ ሲናገሩ "ያንተ ብቸኛ ዓላማ የተሻለ ሕይወትን ከሚፈልጉ ሰዎች ላይ የምትችለውን ያህል ከፍተኛ ገንዘብ መሰብሰብ ብቻ ነበር" ብለዋል።

በሰሜናዊቷ የኔዘርላንድስ ከተማ ዝዎለ የሚገኘው ፍርድ ቤት፣ የዘራፊ ቡድን አባላት በኔዘርላንድስ የሚገኙ ቤተሰቦችን በስልክ እያሰሙ ሰዎችን ግርፊያ ይፈጽሙባቸው እንደነበር ሰምቷል። ቤተሰቦቹ ስቃዩ እንዲቆም ክፍያ እንዲፈጽሙ ይጠየቁ ነበር ብሏል።

ቤተሰቦቻቸው ገንዘቡን ካስተላለፉ በኋላ ብቻ ነው ተጎጂዎቹ አደገኛ ለሆነው የሜዲትራኒያን ባሕር ጉዞ ብቃት በሌላቸው ጀልባዎች ላይ እንዲጫኑ የሚደረገው። በዚህ የባሕር ጉዞ ላይም ብዙዎች ሰጥመው ቀርተዋል።

ዐቃቤ ሕግ ግለሰቡን በሰዎች መነገድ፣ በማስፈራራት ገንዘብ መቀበል፣ ታጋቾችን መያዝ እና ፆታዊ ጥቃት ወንጀሎችን የመፈጸም ዓላማ ያለውን የወንጀል ቡድን በመምራት ከሶታል። በዚህም ምክንያት የ20 ዓመት ከፍተኛ የእስራት ቅጣት እንዲበየንባቸው ጠይቀዋል።

ዳኛ ሜላርድ በበኩላቸው ሲናገሩም "የወንጀሎቹ አሰቃቂነት እና መጠነ-ስፋት የ20 ዓመት የእስራት ቅጣትን ተገቢ ያደርጉታል" ብለዋል።

ተጨማሪ ለማንበብ:- https://www.facebook.com/share/1DUaM9vTvo/