Addis Standard Amharic
17.9K subscribers
4.87K photos
123 videos
3 files
3.87K links
አዲስ ስታንዳርድ በጃኬን አሳታሚ ኃ.የተ.የግ.ማ. ባለቤትነት ስር የሚታተም በኢትዮጵያ የሚገኝ ነፃ እና ገለልተኛ ሚዲያ ነው። አዲስ ስታንዳርድ አማርኛ የአዲስ ስታንዳርድ እንግሊዝኛ ሕትመት አካል ነው።
ፌስቡክ: https://rb.gy/xwxb3
ትዊተር (X)፡ https://rb.gy/34uh4
Download Telegram
ጥልቅ ትንታኔ፡ የ #አዲስአበባ ኮሪደር ፕሮጀክት ሁለት ገጽታዎች፤ የለውጥ እና የመፈናቀል ታሪኮች

አዲስ አበባ ከተማ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ስፋቱ 2 ሺህ 817 ሄክታር እና 132 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ቦታ ላይ የሚገነባ የሁለተኛ ዙር የኮሪደር ፕሮጀክት ስራን እያከናወነች ትገኛለች። በርካታ አላማዎችን አንግቦ የተጀመረው ፕሮጀክቱ በነጋዴዎች እና ነዋሪዎች ላይ ተጽዕኖ አድርሷል በሚል ትችት እየቀረበበት ይገኛል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የረር አካባቢ ነዋሪ፤ ሁለተኛውን ምዕራፍ የኮሪደር ፕሮጀክት ተከትሎ “ያለምንም ቅድመ-ማስጠንቀቂያ በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት ባርና ሬስቶራንት እንደፈረሰባቸው” ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

የፈረሰባቸው ቦታ 221 ካሬ ሲሆን ምትክ ለሲጠቸው ቃል የተገባው ግን 150 ካሬ ብቻ መሆኑን ጠቅሰው ካሳም እንዳልተሰጣቸው ገልጸዋል።

የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሁለተኛውን ምዕራፍ በኮሪደር ፕሮጀክቱ ለሚነሱ የግል ባለይዞታዎችም 5 ቢሊየን ብር የሚደርስ ካሳ በጀት መያዙን በመግለጽ 100 ሄክታር የሚጠጋ ምትክ መሬትና የሁለት አመት የቤት ኪራይ ክፍያም እንደተዘጋጀላቸው ገልጸዋል፡፡ ለልማት ተነሺ ደግሞ መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ መስሪያ ቦታዎች የንግድ ቤቶችና ሱቆች መሰራታቸውንም አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ አዲስ ስታንዳርድ ጋር ቆይታ ያደረጉት እና ስማቸውም ሆነ የንግድ ቤታቸው መጠሪያ እንዳይጠቀስ የጠየቁ ነዋሪ በበኩላቸው ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ፣ ካሳ እና ምትክ ቦታ እንዲነሱ መደረጋቸውን ይገልጻሉ።

ሙሉ ዘገባውን ያንብቡ፦ https://addisstandard.com/Amharic/?p=6464
ዜና: #የሶማሊያን አንድነት እና ሉአላዊነት የሚጋፋ ተናጠላዊ አርምጃን በጋራ እንከላከላን ሲሉ ግብጽ እና ኤርትራ አስጠነቀቁ

#የግብጽ#ኤርትራ እና ሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሀገራቱ መካከል በመሪዎች ደረጃ በተደረሱ ስምምነቶች ዙሪያ ጥር 3 ቀን 2017 ዓ.ም በካይሮ ውይይት ማካሄዳቸው ተገለጸ።

ውይይታቸው መጠናቀቁን ተከትሎ ሚኒስትሮቹ በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ የግብጹ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ የሶማሊያን አንድነት እና ሉአላዊነት የሚጋፋ ተናጠላዊ አርምጃን በጋራ እንከላከላን ሲሉ መናገራቸውን ከአህራም ጋዜጣ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

"ለሶማሊያ መረጋጋት፣ ደህንነት እና የግዛት አንድነት ያለንን ቁርጠኝነት እናረጋግጣለን፤ እንዲሁም የሶማሊያ መንግስት በአጠቃላይ የሀገሪቱ ግዛቶች ላይ የሚያካሂደውን ቁጥጥር እንደግፋለን፤ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የሚያደርገውን ጥረትም እናግዛለን” ብለዋል።

የ3 ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጥር 3 ቀን ያካሄዱት የጋራ ውይይት የሀገራቱ መሪዎች በአስመራ ያካሄዱትን ውይይት ተከትሎ የተካሄደ የመጀመሪያው ስብሰባ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው ግዜውን የጠበቀና ቀጣይነት ያለው ውይይቶች ለማድረግ መስማማታቸውን አስታውቋል

ቀጣዩ ስብሰባቸው በሞቃዲሾ እንደሚሆን አመላክቷል።

የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር “በቀይ ባህር ዳርቻ የድንበር ወሰን የሌላቸው ሀገራት የባህር ሀይልም ሆነ ማንኛውም ወታደራዊ ሰፈር ማቋቋም ተቀባይነት አይኖረውም” ሲሉ በድጋሚ ማስጠንቀቃቸውንም ዘገባው አካቷል።

ከሶስትዮሽ ውይይታቸው በተጨማሪም የግብጹ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኡስማን ሳላህ እና ከሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ ፊቂ ጋር በተናጠል ውይይት ማድረጋቸውም ተጠቁሟል።

በቅርቡ የሀገራቱ መሪዎች ሁለተኛውን ስብሰባቸውን እንደሚያካሂዱም ተጠቁሟል።
ዜና: ኮሚሽኑ በ #ኦሮሚያ እና #አማራ ክልሎች ሲንቀሳቀሱ ለነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና መሥጠት መጀመሩን አስታወቀ

ብሔራዊ የተሀድሶ ኮሚሽን በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ሲንቀሳቀሱ ለነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና መሥጠት መጀመሩን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል "ጥያቄዎቻቸዉን በሀይል ለማሳካት ታጥቀዉ ሲንቀሣቀሱ የነበሩ" ያላቸውና በቅርቡ ከክልሉ መንግስት ጋር የሰላም ስምምነት በመፈፀም በማዕከላት ከተሰባሰቡት መካከል በ #አዋሽ ቢሾላ የተሃድሶ ማዕከል ለሚገኙ የቀድሞ ተዋጊዎች የተሃድሶ ሥልጠና መስጠት መጀመሩን ገልጿል።

በተመሳሳይ በአማራ ክልልም የቀድሞ ታጣቂዎች የተሐድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ይፋዊ የማስጀመሪያ ሥነ-ስርዓት በ #ቡርቃ የዲሞብላይዜሽን ማዕከል ተካሄዷል።

https://addisstandard.com/Amharic/?p=6485
ዜና፡ በ #ሞያሌ የ14 አመት ታዳጊ ላይ የተፈጸመው ግድያ ቁጣ አስነሳ፤ በመንግስት ጽ/ ቤቶች ላይ ውድመት መድረሱ ተገለጸ

#ኦሮሚያ ክልል #ቦረና ዞና በሞያሌ ከተማ ሸዋ ባር ቀበሌ የ14 አመት ታዳጊ “በፖሊስ አባላት” መገደሉ በነዋሪዎች ዘንድ ቁጣ ቀስቅሷል። ታዳጊው የተገደለው ባለፈው አርብ ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም "በፖሊስ ኃይሎች" በተተኮሰ ጥይት መሆኑ ተገጿል።

ግድያውን ተከትሎ የከተማው ህዝብ ባለፈው ቅዳሜ ተቃውሞ ሰልፍ የወጡ ሲሆን ፖሊስ ሰልፈኞቹን ለመበተን ተኩስ ከፍቶ በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የሞያሌ ከተማ ኮሚኒኬሽን ትናንት ባወጣው መግለጫ፤ በታዳጊው ላይ የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ ሰልፍ መካሄዱን ጠቅሶ "ጽ/ ቤቶችን ሰብሮ በመግባት የማውደም እና በእሳት የማቃጠል" ተግባር መፈጸሙን ገልጿል። ይህም ትክክል አለመሆኑንና የሰልፉን አላማ የምይወክል ነው ብሏል።

https://addisstandard.com/Amharic/?p=6488
ዜና: #የትግራይ ተፈናቃዮች ችግራቸው እየተባባሰ እንደሚገኝ በመግለጽ ወደ ቀያችን መልሱን ሲሉ በሰላማዊ ሰልፍ ጠየቁ፣ ለሶስት ቀናት የሚካሄድ ነው ተብሏል

በትግራይ ከተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ጋር በተያያዘ ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ የክልሉ ነዋሪዎች ችግራቸው እየተባባሰ እንደሚገኝ በመግለጽ ወደ ቀያችን መልሱን ሲሉ በሰላማዊ ሰልፍ መጠየቃቸው ተገለጸ።

#መቀለ ከተማ ዛሬ ጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም የተጀመረው ሰላማዊ ሰልፉ ለሶስት ቀናት እንደሚካሄድ ተጠቁሟል፤ በሰልፉም ተፈናቃዮች ወደ ቀያችን በአስቸኳይ መልሱን ብለዋል።

“ይበቃል” በሚል መሪ ቃል ሰላማዊ ሰልፉን ያዘጋጀው “ጽላል ለምዕራብ ትግራይ” የተሰኘ የሲቪል ማህበረስ ድርጅት ሲሆን ዋነኛ አላማውም ተፈናቃዮች እያጋጠማቸው ላለው የከፋ ችግር ግንዛቤ ለመፍጠር ነው ተብሏል።

በመቀለ ከተማ ሮማናት አደባባይ የተጀመረው ሰላማዊ ሰልፉ በአለምአቀፍ ደረጃ ለማካሄድ ለታሰበው “ይበቃል” ንቅናቄ አካል መሆኑም ተገልጿል።

https://addisstandard.com/Amharic/?p=6490
#ሶማሊያ #ኢትዮጵያን #በአውሶም ወታደሮች ኮታ ውስጥ ለማካተት እየሰራች መሆኑን ገለጸች

ሶማሊያ ከዲፕሎማሲያዊ መሻሻል በኋላ ኢትዮጵያን በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ (አውሶም) ወታደሮች ኮታ ውስጥ ለማካተት እየሰራች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አሊ መሃመድ ኦማር አስታወቁ።

ሚኒስትር ዴኤታው የተወሰኑ መሻሻሎች ቢደረጉም፣ ቀደም ሲል በተመደበው ኮታ ምክንያት የኢትዮጵያን ተሳትፎ በማረጋገጥ ረገድ ተግዳሮቶች መኖራቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል።

"ዋነኛው እንቅፋት ከመግባቢያ ስምምነቱ ጋር የተያያዘ ነበር፤ ይህ ጉዳይ ተፈትቷል" ብለዋል። ይሁን እንጂ "አሁን ያለው ተግዳሮች አብዛኛው የወታደሮች ኮታ ቀደም ሲል የተመደበ መሆኑ ነው እናም ለማሰረማራት የቀረው በጣም ጥቂት ነው። መፍትሄ ለመፈለግ በንቃት እየሰራን ነው" ሲሉ አሊ መሃመድ ገልጸዋል።

ይህ የሆነው በቅርቡ በሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሐሙድ እና በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መካከል በአዲስ አበባ በተደረገው ውይይት ሙሉ የዲፕሎማሲ ትስስርን ለመመለስ ስምምነት ላይ መደረሱን ተከትሎ ነው። ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የባህር በር መግባቢያ ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ ከሶማሊያ ጋር የነበራት ግንኙነት መሻከሩ ይታወቃል።

የሶማሊያ ልዑካን ቡድን የጦር ሰራዊት ቁጥርን ጨምሮ የቴክኒክ ዝርዝሮችን ለማጠናቀቅ እና ከሶማሊያ ብሔራዊ ጥቅሞች ጋር የተጣጣመ መሆኑን ለማረጋገጥ ወደ ኢትዮጵያ ለማምራት ቀጠሮ ተይዟል።

በተጨማሪም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አሊ መሃመድ፤ ኢትዮጵያ በሶማሊያ አምባሳደሯን ትሾማለች ተብሎ እንደሚጠበቅ እና የሶማሊያም አምባሳደር በቅርቡ በይፋ ሥራውን እንደሚጀምር አረጋግጠዋል። ይህም የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን ለማጠናከር ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያሳያል ሲል ሂራን ዘግቧል።
ዜና: #ነዳጅ ጭነው ተደብቀው የነበሩ ከ200 በላይ ቦቴዎች እና 19 ማደያዎች ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ቅጣት ተጣለባቸው፣ ለ6 ወራት በነዳጅ ግብይት እንዳይሳተፉም ታግደዋል

“በሀገሪቱ የነዳጅ አቅርቦት ችግር ሳይኖር” እጥረት እንዲከሰት እየተደረገ ያለው ሆን ተብሎ ሰራሽ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር ለማድረግ ነው ሲል መንግስት ገለጸ፤ በማሳያነትም ጫካ እና ዱር ውስጥ ተደብቀው የነበሩ 250 የሚጠጉ ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎችን መያዙን ጠቁሟል።

ቦቴዎች ከ10 እስከ 15 ቀናት ጫካ እና ዱር ውስጥ ቆመው እንደነበር የጠቆመው መንግስት ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት እና በተክኖሎጂ በመታግዘ መያዝ ተችሏል ሲሉ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ትላንት ጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ አመላክተዋል፡፡

ቦቴዎቹና 19 ተባባሪ ማደያዎች ለ6 ወራት በነዳጅ ግብይት ውስጥ እንዳይሳተፉና ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ቅጣትም እንደተጣለባቸው ጠቁመዋል።

መንግስት በሀገሪቱ በሽያጭ ላይ የሚገኘው ነዳጅ በአለም አቀፍ ደረጃ ካለው ዋጋ ባነሰ ነው እየሸጠ ያለው ሲሉ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፤ ለዚህም በርካታ ቢሊዮን ብር በመመደብ እየደጎመ ነው ብለዋል።


በአሁኑም የዋጋ ማስተካከያ ከዓለም ዋጋ አንፃር ምንም ትርፍ ሳይያዝበት መተላለፍ ከነበረበት ዋጋ ለቤንዚን 21 ብር ለናፍጣ ደግሞ 28 ብር እየደጎመ ነው፤ ጫናውን መሸከሙን ህብረተሰቡ ይወቅለት ብለዋል።

https://web.facebook.com/AddisstandardAmh/posts/pfbid02xkSUEhRJSrku5q4FdV538d5cVbCjm5yK3CHDX4vPT5nZVd5YYworQ7wrcqHNPf7jl
የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ መምህሩ ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) በአቶ መሐመድ እድሪስ ምትክ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር እንዲሆኑ የቀረበለትን ሹመት አፀደቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ መምህር፣ የኮሚኒኬሽን እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም በዩንቨርስቲው የማርኬቲንግና ኮሚኒኬሽን ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑትን ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) የባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር እንዲሆኑ በእጩነት አቅርበዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 15ኛ መደበኛ ጉባዔ ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው እንዲሾሙ የቀረበለትን ጥያቄ አፅድቋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ መሐመድ እድሪስ የሰላም ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ይታወቃል።
ዜና: የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በርካታ ትችቶችን ሲያስተናግድ የነበረውን #የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅን አፀደቀ

ቋሚ ገቢ ባላቸው ዜጎች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳድራል በሚል ስጋትና ትችት ሲቀርብበት የነበረው የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ጥር 6 ቀን 2017 ዓ.ም ቀርቦ ጸደቀ።

በአዋጁ በተደነገገው መሰረት ለማንኛውም ንብረት የሚከፈለው ታክስ መጠን ከንብረቱ የገበያ ዋጋ ወይም ምትክ ዋጋ 25 በመቶ እንዲሆን ተደርጓል።

"ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የከተማ ንብረት ዋጋ በበቂ ሁኔታ ታክስ እየተጣለበት ባለመሆኑ የመንግስት የገቢ ላይ እጥረትን አስከትሏል" ፤ "ይህም ሁኔታ በከተሞች ውስጥ ያለውን ያልተጣጣመ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ላይ አስተዋጽኦ አድርጓል" ሲሉ የዕቅድ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ በምክር ቤቱ ተገኝተው ለአባላቱ በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል።

የፓርላማ አባላት በበኩላቸው ቋሚ ገቢ ባላቸው ዜጎች እና የመንግስት ሰራተኞች ላይ ከዚህ ቀደም የተጣሉ ታክሶች ላይ ሌላ ተጨማሪ ግብር እንዲከፍሉ መደረጉ ከፍተኛ ስጋት ይፈጥራል ሲሉ አሳስበዋል።
https://addisstandard.com/Amharic/?p=6501
#ኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር መስመር ስራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ትርፍ ማስመዝገቡ ተገለጸ

የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር መስመር ስራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2024 የመጨረሻው ሩብ ዓመት ትርፍ ማስመዝገቡን የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) ገለጹ፡፡

"ይህ ስኬት ኩባንያውን አትራፊ ለማድረግ የተያዘው የሦስት ዓመት ስትራቴጂያዊ እቅድ እንደሚሳካ ማሳያ ነው።" ሲሉ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ለጠንካራ ትርፋማነት መሰረት በመጣሉ ቀጣይ ጉዞው ወደ ላቀ ስኬት መሆኑን አመልክተዋል።

ይህ የተገለጸው ዋና ሥራ አስፈጻሚው ኩባንያውን በሦስት ዓመታት ውስጥ ወደ ትርፋማነት ለመቀየር ቃል ከገቡ ከአምስት ወራት በኋላ መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) በወቅቱ አስፈላጊ ለውጦችን እና ትርፋማነትን ለማስመዝገብ የሶስት አመት ስትራቴጂክ እቅድ እና አዲስ ድርጅታዊ መዋቅር እንደተዘጋጀ መግለጻቸው ይታወሳል።

ባሳለፍነው አመት ነሃሴ ወር ታከለ ኡማ (ኢ/ር) አጠቃላይ ካሉ 32 የጭነት ባብሮች ውስጥ በስራ ላይ ያሉት 15ቱ ብቻ መሆናቸውን በመግለጽ የባቡር መስመሩ ያለበት ሁኔታ እንዳሳሰባቸው ገልጸው ነበር። ይህም አመታዊ የመጫን አቅምን በእጅጉ የሚቀንስ ነው ብለዋል። አቅሙ በአመት 6.3 ሚሊዮን ቶን መድረስ ያለበት ቢሆንም አሁን ላይ እየተከናወነ ያለው በአመት 2.4 ሚሊዮን ቶን ብቻ ነው ይህም የሙሉ አቅሙ 38 በመቶ ብቻ ነው ብለዋል።
ዜና: “#የፕሪቶርያው ስምምነት መሰረታዊ ጉዳዮች በአግባቡ ባለመተግበራቸው የትግራይ ህዝብ አንድነት ፈተና ላይ ወድቋል” - የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር

ተፋናቃዮች እያካሄዱት ያለው ሰላማዊ ሰልፍ የሚደገፍ ነው ብሏል


“ይበቃል” በሚል መሪ ቃል ትላንት ጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም በመቀለ ከተማ የተጀመረው በ #ትግራይ ክልል ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ የክልሉ ነዋሪዎች እያካሄዱት ያለውን ሰላማዊ ሰልፍ የክልሉ ግዜያዊ አስተዳደር እንደሚደግፈው አስታወቀ።

የፕሪቶርያ ስምምነቱ አስገዳጅ እና ዋነኛ ሁኔታዎች አልተተገበሩም ሲል የኮነነው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ባወጣው መግለጫው እነዚህ ጉዳዮች አለመፈጸማቸው “ህዝባችን አስቸጋሪ እና ውስብስብ ሁኔታ ውስጥ” ከቶታል” ብሏል።

“በተለያዩ ሃይሎች ስር ያለው ህዝባችን አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰቃዩ ነው፣ የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ወደ ቤታቸው መመለስ ባለመቻላቸው ኢሰብአዊ ሕይወት እየኖሩ ነው” ያለው መግለጫው “ከስምምነቱ መንፈስ በተቃራኒ የትግራይ ሕገ መንግሥታዊ የግዛት አንድነት አደጋ ላይ ነው” ሲል አትቷል።

የፌደራል መንግስት እስካሁን ያልተፈጸሙ የፕሪቶሪያ ስምምነትን ዋነኛ ጉዳዮችን እንዲያስፈጽም በመግለጫው የጠየቀው ጊዜያዊ አስተዳደሩ “በተለያዩ ሀይሎች ስር እየተሰቃዩ ያሉትን ወገኖቻችንን ነፃ በማውጣት” ፣ “ከቀያቸወ የተፈናቀሉ የክልሉ ነዋሪዎችን ወደ ቤታቸው በመመለስ” ፣ “የትግራይ ህገመንግስታዊ የግዛት አንድነተን በማስከበር እንዲሁም ተጠያቂነት በማስፈን ህጋዊና ሞራላዊ ሃላፊነቱነ ሊወጣ የገባል” ሲል አሳስቧል።
https://addisstandard.com/Amharic/?p=6504
ሙሉ ግንባታው ሊጠናቀቅ 2.4 በመቶ ብቻ የቀረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቀሪ ስራዎችን ለማጠናቀቅ 80 ቢሊዮን ብር ያስፈልገዋል ተባለ

ሙሉ ግንባታው ሊጠናቀቅ 2.4 በመቶ ብቻ የቀረው ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ቀሪ ስራዎች ለማጠናቀቅ 80 ቢሊዮን ብር ያስፈልገዋል ያስፈልገዋል መባሉን ሸገር ሬድዮ ዘግቧል።

ግንባታው 97.6 በመቶ እንደደረሰና ጥቂት የማጠናቀቂያ ስራዎች ብቻ እንደቀሩት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ የፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ተናግሯል ተብሏል፡፡

ከ14 ዓመት አመታት በፊት የግንባታው መሰረት ድንጋይ ሲጣል 80 ቢሊዮን ብር ያስፈልገዋል ተብሎ የተጀመረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ፤ የ2.4 በመቶ ስራም ቀርቶት ለምን 80 ቢሊዮን ብር እንዳስፈለገ በብዙዎች ጥያቄን ጭሯል።

በጉዳዩ ዙሪያ የህዳሴ ግድብን የቦንድ ሽያጭ ሲከውን የቆየውን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የካፒታል ገበያ ዳይሬክቶርት ዳይሬክተር አቶ ዳዊት አማረ ከሸገር ሬድዮ ለቀረበላቸው ጥያቄ የግንባታ ስራው በተለያ ደረጃ ስለሚመራ ስለዚህ ጉዳይ ፕሮጀክቱን የሚመሩት የስራ ሃላፊዎች ናቸው የሚያውቁት ብለዋል፡፡

ይሁንና ልማት ባንክ የቦንድ ሽያጭ ላይ እንደመሳተፉ እስካሁን ከህዝቡ ከ20.2 ቢሊየን ብር በላይ መዋጣቱን መናገር እንችላለን ብለዋል፡፡ ለማጠናቀቂያ ስራው ከሚያስፈልገው ገንዘብ ልማት ባንክ 10 ሚሊዮን ብር መስጠቱንም አቶ ዳዊት ተናግረዋል፡፡

ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤቱ በበኩሉ በዚህ ዓመት እስከ 1.6 ቢሊዮን ብር ከህዝቡ ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል፡፡
#አውሮፓህብረት#ኢትዮጵያ ለሰብአዊ እርዳታ የሚውል የ40 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ለማድረግ ማቀዱን ገለጸ

የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ "ግጭቶች፣ ተደጋጋሚ የአየር ንብረት ለውጦች እና ተላላፊ በሽታዎች" ያሳደሩትን ተፅእኖ በመጥቀ በጎርጎሮሳውያኑ 2025 ዓ.ም 40 ሚሊዮን ዩሮ የመጀመሪያ የሰብአዊ እርዳታ ለመመደብ ማቀዱን አስታውቋል።

ይህ ድጋፍ ከ2020 ጀምሮ ለኢትዮጵያ የተደረገውን አጠቃላይ የሰብዓዊ ድጋፍ 436.5 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚያደርሰውም ገልጿል።

የአውሮፓ ህብረት እንደገለፀው ድጋፉ፤ "የጥበቃ፣ የምግብ እርዳታ፣ ንጹህ ውሃ እና ንፅህና፣ መጠለያ እና የተመጣጠነ ምግብ እርዳት" አቅርቦትን በማድረስ ረገድ የበጎ አድራጎት አጋሮችን ይደግፋል። በተጨማሪም በሽታዎችን መከላከል፣ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ጥበቃ እና በቀውሶች ለተጎዱ ህጻናት ትምህርትም እንደሚውልም ተገልጿል።

እርዳታው ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና በተለይም እንደ ሱዳን ካሉ ጎረቤት ሀገራት አዲስ ለስደተኞች ሰዎች በቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑን የገለጸው የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያን አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ ለማሟላት ያለውን ቁርጠኝነት አፅንዖት ሰጥቷል።

================
የአዲስ ስታንዳርድ አማርኛ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ይቀላቀሉ፡
ቴሌግራም: https://rb.gy/rekjr
ፌስቡክ: https://rb.gy/xwxb3
ትዊተር (X)፡ https://rb.gy/34uh4
ዩቲዩብ፡ https://rb.gy/bjcbg
ድረገጽ: https://rb.gy/5td6n
ቲክቶክ፡ https://rb.gy/jgdsjm
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ “ተገቢ ያልሆነ” ሰልፎችን የሚፈጥሩ ማደያዎችን "በፍጹም እንደማይታገ" እና ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ “ተገቢ ያልሆነ” ሰልፎችን የሚፈጥሩ ማደያዎችን "በፍጹም እንደማይታገ" ና ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ።

የቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ ትናንት ጥር 6/2017 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ፤ ነዳጅን በጥሬ ገንዘብ ሽያጭ የሚፈጽሙ፣ የነዳጅ እጥረትን በሚፈጥሩ እና የ24 ሰዓት አገልግሎት በማይሰጡ መሰል ድርጊቶች ላይ በሚሳተፉ ማደያዎች ላይ እርምጃዎች እንደሚወሰድ አሳስበዋል፡፡

ኃላፊዋ ናፍጣ በከተማዋ 125 ማደያዎች ቀርቦ በመሰራጨት ላይ በአማካኝ በቀን 2 ሚሊዮን ሊትር፣ ቤንዚን በአማካኝ በቀን 1.45 ሚሊዮን ሊትር በድምሩ ባለፉት ስድስት ወራት በቀን በአማካኝ 3.45 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ በበቂ መጠን መቅረቡን አመላክተዋል፡፡

“በከተማዋ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ምንም አይነት የነዳጅ እጥረት እንዳልነበር” አክለው ገልጸዋል።

በቁጥጥር ሂደት ህገ-ወጥ ተግባር ውስጥ የገቡ ነዳጅ ማደያዎች ላይም እርምጃ መወሰዱን ያስታወሱት የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ በዚህም በህገ-ወጥ ሲዘዋወር የተወረሰ 47608.5 ሊትር ነዳጅ ምርት ተሽጦ 2,600,649.94 ብር ለመንግስት ገቢ መደረጉም አውስተዋል፡፡

================
የአዲስ ስታንዳርድ አማርኛ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ይቀላቀሉ፡
ቴሌግራም: https://rb.gy/rekjr
ፌስቡክ: https://rb.gy/xwxb3
ትዊተር (X)፡ https://rb.gy/34uh4
ዩቲዩብ፡ https://rb.gy/bjcbg
ድረገጽ: https://rb.gy/5td6n
ቲክቶክ፡ https://rb.gy/jgdsjm
አገልግሎቱ በስድስት ወራት 16 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡንና ከ13 ሺህ በላይ ዜጎች ላይ እርመጃ መውሰዱን አስታወቀ

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ባለፋት ስድስት ወራት 10 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ከ16 ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ዛሬ በሰጡት መግለጫ፣ በሐሰተኛና በተጭበረበሩ የጉዞ ሰነዶች አገልግሎት ለማግኘት ሲንቀሳቀሱ በነበሩ 13,322 ዜጎች ላይ አሰተዳደራዊ ርምጃ መወሰዱንም ገልጸዋል።

ከ721 ሺህ 623 በላይ ፓስፖርቶችን የማተም ስራ ተሰርቷል ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ ከታተመው 98 በመቶው ለተገልጋዮች ተሰጥቷል ብለዋል።

ለ14 ሺህ 367 ለሚሆኑ የውጭ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የመኖሪያ ፍቃድ የመስጠት ስራ መከናወኑንና በዚህም ለ20 ግለሰቦች ዜግነት እንደተሰጣቸውም አብራርተዋል። ለዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሠው ሀይሉን የማጠናከር፤ አሰራሩን በቴክኖሎጂ የማገዝ ስራ ይሰራልም ብለዋል።

አገልግሎቱ በ2016 በጀት ዓመት የሰበሰበው ገቢ 14 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ሲሆን ለ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ተገልጋዮች ፓስፖርት መሰጠቱም ይታወሳል።
'መስፈርት አላሟሉም' በሚል 400 የሚሆኑ ሠራተኞች ከሥራ ተባረሩ

የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት "በድልድል እና ምደባ" 400 የሚሆኑ ሠራተኞችን ከጥር ጀምሮ ከሥራ ማሰናበቱን ሠራተኞች እና ድርጅቱ ተናገሩ።

በ2015 ዓ.ም. "የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት" በሚል ከ70 ዓመታት በላይ ለአዲስ አበባ የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው አንበሳ ባስ እና ሸገር ብዙኃን ትራንስፖርት ተዋህደው የልማት ድርጅት ተመሥርቷል።

ይህን ተከትሎ "ሪፎርም" ማድረግ የጀመረው ድርጅቱ፤ ባከናወነው ድልድል እና ምደባ ሠራተኞች "ያለአግባብ" እና "በዘፈቀደ" ከሥራ ተባረናል ሲሉ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት የብቃት ፈተና እና ውድድር ያላለፉ ሠራተኞችን ከሥራ መቀነሱን በመግለፅ "የሪፎርም ባሕሪ ነው" ሲል ለቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ምላሽ ሰጥቷል።

ለሠራተኞቹ መመሪያውን ሲያስተዋውቅ የብቃት ፈተና ሰጥቶ ፈተናውን ባያልፉ እንኳ አንድ የደረጃ እርከን ዝቅ ተደርገው ሥራቸውን እንደሚቀጥሉ መተማመኛ መስጠቱን ተናግረዋል።

ተቋሙ ይህን ቢልም ፈተናውን ያለፉም ያላለፉም፤ የትምህርት እና የሥራ ልምድ ያላቸው ሠራተኞችን "ያለምንም ማስጠንቀቂያ" ከሥራቸው እንዳባረረ ስድስት ሠራተኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከሥራ የተሰናበቱት ሠራተኞች ከፅዳት እና የጥበቃ ሠራተኞች ጀምሮ በተቋሙ ለአስርት ዓመታት ያገለገሉ እና የጡረታ ዕድሜያቸው የተቃረቡ ሠራተኞችም እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

https://www.bbc.com/amharic/articles/cly5757l54go
ዜና፡ በ #ምስራቅ_ሀረርጌ ዞን ኩርፋ ጨሌ ወረዳ ሁለት ወጣቶች “በሚሊሻዎች” መገደላቸውን የቤተሰብ አባላት ተናገሩ

#ኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሀረርጌ ዞን ኩርፋ ጨሌ ወረዳ ጥር 5 ቀን 2017 ዓ/ም ከማያ ከተማ ሞተር ሳይክል ገዝተው ወደ ጉራዋ ወረዳ በመመለስ ላይ የነበሩ ሁለት ወጣቶች “በጸጥታ ኃይሎች” በተተኮሰባቸው ጥይት መገደላቸውን ቤተሰቦቻቸው ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

ግድያው የተፈጸመባቸው ወጣቶች ከዲሬ ሹኢቤ እና ጃፋር አብዱራዛቅ የተባሉ የጉራዋ ወረዳ ላፍቶ ቀበሌ ነዋሪ እንደሆኑ ቤተሰቦቹ ገልጸዋል።

“ሚሊሻዎቹ በጥይት ካቆሰሏቸው በኋላ እዚያው ተተዋቸው እንደሄዱ” የተናገሩት የቤተሰቡ አባሉ፤ “በኋላም የአካባቢው ማህበረሰብ አምቡላንስ ጠርቶ ወደ ጉራዋ ሆስፒታል ቢወስዳቸውም ሊተርፉ አልቻሉም” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ አስረድተዋል።

ያንብቡ፦ https://addisstandard.com/Amharic/?p=6510
#በፎቶ፡ በ #አፋር ክልል በተለይ በ #አዋሽ እና #ዱለቻ ወረዳ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ባለው የመሬት መንቀጥቀጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው እንዲፈናቀሉ አስገድዷል።

ተፈናቃዮቹ እየተደረገላቸው ያለው የውሃ እና የምግብ እርዳታ በመጠለያ ጣቢያው ካሉ የተፈናቃዮች ብዛት አንጻር በቂ አይደለም አለመሆኑን ይገልጻሉ። የውሃ እጥረት ዋነኛው ችግር ሲሆን በተሽከርካሪዎች የሚቀርብላቸው የውሃ አቅርቦት ከተቋረጠ በኋላ ባልታከመ የወንዝ ውሃ ላይ ጥገኛ በመሆናቸው በበሽታ የመያዝ ስጋትን ጨምሯል።

በክልሉ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ባለው የመሬት መንቀጥቀጥ ከሰም ስኳር ፋብሪካን ጨምሮ በርካታ መኖሪያ ቤቶችን እና መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት አድርሷል።

በዚህም 4 ሺህ የከሰም ሱካር ፋብሪካ ሰራተኞችን ጨምሮ ከ58 ሺህ በላይ ሰዎች ጊዜያዊ መጠለያ ገብተው ሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑም ክልሉ አስታውቋል።

ፎቶ፡ ለአዲስ ስታንዳርድ (ከአሚበራ ወረዳ ዳኢዶ የመጠለያ ጣቢያ)