Addis Standard Amharic
17.9K subscribers
4.87K photos
123 videos
3 files
3.87K links
አዲስ ስታንዳርድ በጃኬን አሳታሚ ኃ.የተ.የግ.ማ. ባለቤትነት ስር የሚታተም በኢትዮጵያ የሚገኝ ነፃ እና ገለልተኛ ሚዲያ ነው። አዲስ ስታንዳርድ አማርኛ የአዲስ ስታንዳርድ እንግሊዝኛ ሕትመት አካል ነው።
ፌስቡክ: https://rb.gy/xwxb3
ትዊተር (X)፡ https://rb.gy/34uh4
Download Telegram
ምክር ቤቱ የመንግስትና የህዝብ ንብረትን የማስመለስ ረቂቅ አዋጅን አጸደቀ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው14ኛ መደበኛ ስብሰባው 10 ዓመት ወደኃላ በመሄድ የመንግስትና የህዝብ ንብረትን የሚያስመልስ አዋጅን አጸደቀ።

አዋጁ በሕገ-ወጥ መንገድ የተፈራን ንብረት ማስመለስ የሚያስችሉና የሕግ-ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ድንጋጌዎችን የያዘ መሆኑና የመንግስትና የህዝብ ንብረትን ለማስመለስ የነበረውን የሕግ ክፍተት የሚሞላ እንደሆነ ተገልጿል።

አዋጁ ዜጎች በላባቸውና በወዛቸው ንብረት እንዲያፈሩ የሚያበረታታ፣ በወንጀል ንብረት የሚያፈሩትን ተጠያቂ የሚያደርግ፣ የአገርን ዕድገት የሚያሳልጥ እንደሆነ አስተያየት የሰጡ የምክር ቤት አባላት አንስተዋል።

ግለሰቦች በወንጀልና በሙስና ያፈሩትን ንብረት የሚያስመልስ በመሆኑ በተፈጻሚነቱ ላይ ጥንቃቄ ማድረግና አስፈጻሚ አካላትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ እና የዜጎችን ንብረት የማፍራት መብት እንዳይጋፋ መታየት አለባቸው ያሏቸውን ጉዳዮችም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዕጸገነት መንግስቱ በአዋጁ ሃብት የማፍራትና የማውረስ ሕገ-መንግስታዊ መብትን የሚቃረን ድንጋጌ አለመካተቱንም አብራርተዋል።

የጸረ-ሙስና ትግል እንዲጠናከር የሚያደርግ፣ በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘና የተመዘበረ የአገር ሃብትን ለማስመለስ የሚያስችልና ሕገ-ወጥነትን የሚያስቆም አዋጅ እንደሆነም አክለው ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ በአዋጁ አስፈላጊነትና ወቅታዊነት ላይ ዝርዝር ውይይት በማድረግ በሶሰት ተቃውሞ እና በአራት ድምጸ ታቅቦ በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁን ዘገባው አመላክቷል።
ዜና: ማንኛውም #የነዳጅ ውጤቶች አጓጓዥ ተሸከርካሪ ጂ.ፒ.ኤስ (መከታተያ) እንዲገጥም የሚያስገድድ አዋጅ ጸደቀ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ጥር 1 ቀን 2017 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ የነዳጅ ውጤቶች ግብይት ሥርዓት ለመደንገግ የተዘጋጀ አዋጅን በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል፤ በሁለት ተቃውሞ እና በአንድ ድምጸ ተአቅቦ።

የጸደቀው አዋጅ የነዳጅ አጓጓዥ ተሸከርካሪዎችን በተመለከተ ባሰቀመጠው ግዴታ መሰረት ማንኛውም የነዳጅ ውጤቶች አጓጓዥ ተሸከርካሪ ጂ.ፒ.ኤስ (መከታተያ) እንዲገጥም ይገደዳል።

የነዳጅ ማደያዎች ያልተቆራረጠ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስገደድ፣ ነዳጅ በማደያ ውስጥ እያለ ያለ በቂ ምክንያት አገልግሎት ያለመቋረጥ የሚል ድንጋጌ በአዋጁ መካተቱም ተገልጿል።

ነዳጅ መንግሥት ከተመነው የመሸጫ ዋጋ በላይ ሲሸጡ የተገኙ ነጋዴዎች እስከ አምስት መቶ ሺህ ብር እንዲቀጡ በአዋጁ ተደንግጓል፤ የነዳጅ ውጤቶችን ከተፈቀደው ቦታ ውጪ ማከማቸትም ያስቀጣል።
https://addisstandard.com/Amharic/?p=6432
ዜና፡ ከ200 በላይ የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ከአንድ ወር በላይ በእስር ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ

#ኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ከ200 በላይ የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች “በህገ ወጥ የእርሻ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል” በሚል ከአንድ ወር በላይ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በእስር ላይ እንደሚገኙ የታሳሪ ቤተሰቦችና ሠራተኞች ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጹ።

ሰራተኞቹ ለስብሰባ ተፈለጋላችሁ በሚል በስብሰባ አዳራሽ ከተሰበሰቡ በኋላ "በህገወጥ መንገድ" በቁጥጥር ስር ውለዋል ሲል ስሙ እንዲገለጽ ያልፈለገ አንድ ሰራተኛ ተናግሯል።

ሌላው የፋብሪካው ሰራተኛ በበኩሉ “በፋብሪካው መሬት ላይ ሰራተኞቹ ካመረቱት 5ሺህ ኩንታል የሚጠጉ የተለያዩ የሰብል አይነቶች ግልፅነት በጎደለው መልኩ ተዘርፏል። ምርቱ ማን እጅ እንደገባ እንኳን አይታወቅም” ብሏል።

ያንብቡ፦ https://addisstandard.com/Amharic/?p=6435
#ኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ በኢትዮጵያ ወደ ምድር ሲንቀሳቀሱ የታዩት የቁስ አካላት ስብስብ የጠፈር ፍርስራሾች አልያም የሚቲዮር አለቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ አስታወቀ

የኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ በትናንትናው ዕለት ከምሽቱ 1፡30 ገደማ በደቡብና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክፍሎች በሰማይ ላይ እየተቀጣጠሉ በከፍተኛ ፍጥነት ሲንቀሳቀሱ የታዩት የቁስ አካላት ስብስብ የጠፈር ፍርስራሾች አልያም የሚቲዮር አለቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ አስታውቋል።

የታየው ስብስብ ወደ ደቡባዊ የሃገሪቱ አቅጣጫ በከፍተኛ ፍጥነት በሰማይ ላይ ሲምዘገዘግ እንደነበረም ለማወቅ ተችሏል ሲል ተቋሙ ገልጿል።

የእነዚህ አካላት ስብስብ ክስተት ተፈጥሮ በእርግጠኝነት ለማብራራት ያስችል ዘንድ ሁኔታውን በቅርበት እያጣራ እንደሚገኝም አክሎ አስታውቋል።

በቅርቡ በኬንያ በማኩኒ ካውንቲ ሙኩኩ በተባለችው መንደር ክብ ቁስ 2 ነጥብ 5 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን 500 ኪሎግራም ክብደት ያለው ግዙፍ ብረት ከሰማይ መወደቁ ይታወቃል።

================
የአዲስ ስታንዳርድ አማርኛ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ይቀላቀሉ፡
ቴሌግራም: https://rb.gy/rekjr
ፌስቡክ: https://rb.gy/xwxb3
ትዊተር (X)፡ https://rb.gy/34uh4
ዩቲዩብ፡ https://rb.gy/bjcbg
ድረገጽ: https://rb.gy/5td6n
ቲክቶክ፡ https://rb.gy/jgdsjm
#አፋር ክልል ጋቢ ዞን በርዕደ መሬት 37 ትምህርት ቤቶች ላይ ሙሉ ለሙሉ እና በከፊል ውድመት ደረሰ

በአፋር ክልል ጋቢ ዞን እየተከሰተ ባለው ተከታታይ ርዕደ መሬት በሶስት ወረዳዎች ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 16 ትምህርተ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ሲወድሙ 21 ትምህርት ቤቶች ደግም ከፊል ጉዳት እንደረሰባቸው የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሃላፊ አቶ አብዱ ሀሰን ያዮ ጉዳቱ የደረሰው በአዋሽ-ፋንታሌ፣ ዱላሳ እና ሓንሩካ ወረዳዎች በሚገኙ 37 ትምህርት ቤቶች እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

አክለውም የክልሉ መንግስት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዳይርቁ በክልል ደረጃ ኮሚቴ በማቋቋም ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በገቢረሱ ዞን ዱለሳ እና አዋሽ ፈንታሌ ወረዳዎች በተደጋጋሚ እየተከሰተ ባለው የመሬት መንቀጥቀጥ ከሰም ስኳር ፋብሪካ ላይ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ጉዳቶችን ያስከተሉ ትላልቅ አደጋዎች መደረሳቸውና የድርጅቱ ኃይል ማከፋፈያ ህንጻ መፍረሱ ተገልጿል። የኤሌክትሪካል እና መካኒካል ጉዳቶችም መደርሳቸውን የፋብሪካው ዋና ስራ አስኪያጅ አሊ ሁሴን ተናግረዋል፡፡

በወረዳዎቹ ከሚገኙ ስምንት ቀበሌዎች የተፈናቀሉ 4 ሺህ የከሰም ሱካር ፋብሪካ ሰራተኞችን ጨምሮ ከ58 ሺህ በላይ ሰዎች ጊዜያዊ መጠለያ ገብተው ሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑም ክልሉ አስታውቋል።
#በፎቶ፡ በ #ሰሜን_ወሎ ዞን በ11 ቀበሌዎች ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የሰብል ክምር በከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ ወደመ

#አማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በዋድላ ወረዳ 11 ቀበሌዎች ጥር 1/2017 ዓ.ም በደረሰው “ምክንያቱ ባልታወቀ” የእሳት ቃጠሎ የ154 አርሶ አደሮች የሰብል ክምር መቃጠሉ ተገልጿል፡፡

የዋድላ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሙሉየ ረታ 4 ሺህ 560 ኩንታል የሚኾን 152 ክምር ላይ የደረሰው ቃጠሎ ጉዳት ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት ጠቁመዋል፡፡

የዋድላ ወረዳ የአደጋ መከላከል እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ጽሕፈት ቤት ቡድን መሪ ምትኩ ሞላ በበኩላቸው እስካሁን ባለው መረጃ 770 የሚኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የጉዳቱ ሰለባ መኾናቸውን መግለጻቸውን አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘግቧል፡፡

ፎቶ፡ አሚኮ
ዜና: በአምስት ወራት #ከዳያስፖራው ከ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ መገኘቱ ተገለጸ

ባለፉት አምስት ወራት ከዳያስፖራው ከሁለት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ከሬሚታንስ መገኘቱን #የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የውጭ ምንዛሬ በገበያ እንዲመራ መደረጉ በሕገወጥ መንገድ ወደ ሀገር ቤት ይገባ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ በባንኮች በኩል እንዲመጣ ማስቻሉ ትልቅ ጥቅም እያስገኘ መሆኑን የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ አመልክተዋል።

በተጨማሪ በዶላር አስቀምጦ በዶላር ማውጣት የሚቻልበት ሥርዓት መዘርጋቱም ለውጤቱ አንዱ ማበረታቻ ሆኗል ማለታቸውን ከኢፕድ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2024 በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት መካከል ከፍተኛውን የሬሚታንስ ገቢ ያገኘችው #ኬንያ መሆናን የአለም ባንክ ይፋ ያደረገው ሪፖርት ያሳያል፤ አራት ነጥብ ስምንት ሚሊየን ዶላር በማግኘት።

#ሶማሊያ 1 ነጥብ 73 ቢሊየን ዶላር በ2024 ያገኘች ሲሆን #ኡጋንዳ አንድ ነጥብ 49 ቢሊየን ዶላር ማግኘቷ ተጠቁሟል፤ #ታንዛንያ#ሩዋንዳ እና #ቡሩንዲ በ2024 ያገኙት የውጭ ምንዛሬ ከ1 ቢሊየን ዶላር በታች መሆኑን አመላክቷል።

ኢትዮጵያ ከዳያስፖራው በሕጋዊ መንገድ ከሚላክ ገንዘብ በየዓመቱ በአማካይ ከ4 እስከ 5 ቢሊዮን ዶላር እያገኘሁ ነው ስትል መግለጿን መዘገባችን ይታወሳል፤ የአለም ባንክ በሪፖርቱ ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2024 ከሬሚታንስ ያገኘችው ገቢ 630 ሚሊየን ዶላር ነው ሲል አስቀምጧል።

ከአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛውን የውጭ ምንዛሬ ከሬሚታንስ የምታገኘው ሀገር ግብጽ መሆኗን የጠቆመው የአለም ባንክ ሪፖርት በ2024 ብቻ 22.65 ቢሊየን ዶላር አግኝታለች ብሏል፤ ናይጀሪያ 19.84 ቢሊየን በማግኘት በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጣለች።