YeneTube
119K subscribers
31.3K photos
483 videos
79 files
3.85K links
መረጃዎችን ለመላክ @Fikerassefa
Download Telegram
ቤተክርስቲያን እንዲሁም ቤቶች ተቃጥለዋል‼️‼️

#በአማራ_ክልል_ኦሮሞ_ብሄረሰብ አስተዳደር ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ከብሔራዊ የጸጥታ ምክር ቤት መግለጫ ተሰጥቷል። መግለጫው በአካባቢው የተፈጠረውን አለመረጋጋት ጠቅሶ "የተከሰተውን የሰላም መደፍረስ ለማረጋጋትና የሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል የፀጥታ አስከባሪ ተቋማት አስፈላጊውን ሕጋዊና ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ" ትእዛዝ አስተላልፏል።

ከሰሞኑ በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የተከሰተው አለመረጋጋት ወደ ሰሜን ሽዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ ተሸጋገሮ የሰው ህይዎት መጥፋቱ፣ ንብረት መውደሙ እና ዝርፊያ መፈፀሙ ተነግሯል።

አቶ ሰማቸው የተባሉ የማጀቴ ከተማ ነዋሪ እንደተናገሩት ከትናንት ጀመሮ በተደራጀ መልኩ የቡድን መሳሪያ የታጠቁ አካላት በንጹሃን ዜጎች ላይ ሲተኩሱ ውለዋል፤ በዚህም 14 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሁለቱ የፖሊስ አባላት ናቸው ብለዋል።

አሁንም ስጋት በመኖሩ ነዋሪው አካባቢውን ለቅቆ ወደ ገጠር ቀበሌዎች እየተሰደደ ነው ያሉት አቶ ሰማቸው በዚህ ሰአት የሚካሄድ ተኩስ የለም ነገር ግን የጸጥታ አካላት ባለመድረሳቸው ስጋት አለን ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪና ስሙን መግለጽ ያልፈለገው ግለሰብ ደግሞ "ከትናንት ጀምሮ ባልተዘጋጀንበት ሁኔታ ከቀያችን ድረስ መጥተው ተኩስ ከፈቱብን ባለን አቅም ስንከላከል ለጊዜው ከሁለታችንም ወገን ቁጥራቸውን የማላውቃቸው ሰዎች ሞተውብናል" ብሏል።

የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደርና ፀጥታ መምሪያ ሃላፊ አቶ ካሳሁን እምቢአለ እንደገለጹት ደግሞ የጸጥታ አካላት በሁሉም ቦታ ደርሰዋል። አስፈላጊ ከሆኑ አካላት ጋርም እየተነጋገርንና ነገሮች ወደ ቀደመ ሰላማቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ እያመቻቸን ነው ሲሉ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ትናንት በነበረው ግጭት አንድ ቤተ ክርስቲያን የተቃጠለ መሆኑን የተናገሩት የመምሪያው ኃላፊው በሌላ አካባቢ ቤተክርስቲያንም የማቃጠል ሙከራ ተካሂዶ ባይሳካም በዙሪያው የሚገኙ ቤቶች ግን ተቃጥለዋል ብለዋል። አጣዬ ላይ የግለሰብ ቤቶች እንደተቃጠሉና ዝርፊያም እንደተፈጸመ አብራርተዋል።

"ኦነግ ያደራጃቸው ናቸው ይህን የፈጸሙት" የሚሉት አቶ ካሳሁን "አላማቸውም ሽብር መፍጠርና ዝርፊያ ማካሄድ ነው" ብለዋል። በዚህ ወቅት በስፍራው የሚገኙት የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አበረ አዳሙ እንደገለጹት ደግሞ በአሁኑ ወቅት ሁሉም አካባቢዎችን ማረጋጋት ተችሏል።

አክለውም ሁኔታውን ዘላቂ ሰላም እንዲኖረው ለማድረግም ከሃይማኖት አባቶችና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ትናንት የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ደብረ ብርሃንም ከፍተኛ የሆነ ህዝብ ጎዳና ወጥቶ ችግሩን ሲቃወም መስተዋሉን ከስፍራው ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ነግረውናል።

ዛሬ በአጣዬ ማጀቴና ካራቆሬ አንጻራዊ መረጋጋት የታየ መሆኑን የተናገሩት አቶ ካሳሁን ከባንኮችና አንዳንድ ተቋማት ውጭ ሌሎች አገልግሎቶች መደበኛ ስራቸውን በመስራት ላይ ናቸው ብለዋል። በስፍራው የመከላከያ ሠራዊትም ደርሷል ብለዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ የሚገኙ 500 የሚሆኑ የአካባቢው ተወላጆች ድርጊቱን በማውገዝ ዛሬ ጠዋት ለሚዲያዎች መግለጫ ሰጥተዋል።

መግለጫውን የሰጡት ተሰብሳቢዎች ተወካይ አቶ ደጀን መንገሻ በአካባቢው የተፈጠረ ግጭት አነሳስቷቸው መሰባሰባቸውን ጠቅሰው መግለጫው በቦታው ላይ እየተፈፀመ ያለውን ግድያ፣ አፈናና ዘረፋን አስመልክቶ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራና ሠላም እንዲመጣ ለመጠየቅ ያለመ እንደሆነ ተናግረዋል።

ካለፉት ሁለት ቀናት ጀምሮ በአጣዬ፣ ማጀቴ፣ ካራ ቆሬ፣ እና በአካባቢው በንፁሃን ላይ የተከፈተው ተኩስ፣ ግድያ፣ ዘረፋና አፈና እንዲቆም መንግስት ፈጣን እርምጃ እንዲወስድ፣ በሕይወትና ንብረት ላይ አደጋ ያደረሱ የተደራጁና የታጠቁ ኃይሎች በአፋጣኝ ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ ጥቃቱን በማውገዝ መንግስት ከህዝብ ጎን እንዲቆም፣ በቦታው በቂ የፀጥታ አካላት ተመድቦ ቦታውን እዲያረጋጋ፣ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አፋጣኝ ሰብዓዊና ቁሳዊ እርዳታ እንዲደርሳቸው ጥሪ ለማቅረብና ሟቾቹንም በፀሎት ለማሰብ ነው ሲሉ ዐብይ የመግለጫውን ይዘቶች ዘርዝረዋል።

አቶ ደጀኔ እንዳሉት በተለይ በማጀቴ፣ ካራ ቆሬ፣ አንፆኪያ አካባቢዎች ከዚህ ቀደምም በግጦሽም ሆነ በውሃ ሲጋጩ፣ በሽማግሌ ሲፈታ የኖረ ነው በማለት ሕዝቦቹ ተሳስበውና ተከባብረው የሚኖሩ ናቸው፤ ነገር ግን "አሁን የተፈጠረው ግን ታስቦበት፣ ታቅዶና ተጠንቶ የተደረገ ነው፤ ተራ ግጭት አይደለም" ሲሉም ያክላሉ።

ስልጠና ተካሂዶ፣ ከግለሰብ የማይጠበቅ መሳሪያ ተታጥቀው፣ ቦታና ምሽግ ይዘው ህዝቡን ሲያጠቁ ነበር የሚሉት ተወካዩ የተደራጀና ሌላ ዓላማ ያለው ኃይል እንዳለ ተረድተናል ብለዋል።

"የክልሉ ልዩ ኃይልም ሆነ መከላከያም የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ገብተዋል ፤ነገር ግን ቦታው ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት የክልሉም ሆነ የፌደራል መንግስት በሚገባው ልክ የተረዱት አይደለም፤ የተላከውም ኃይል በቂ አይደለም" ሲሉ የጉዳዩን አሳሳቢነት ያስረዳሉ።

አሁንም በአጣዬ ዙሪያ አላላ የተባለው አካባቢ የታጠቁ ኃይሎች ጥቃት እያደረሱ እንደሆነ መረጃ እንደደረሳቸውም ነግረውናል።

"ሕዝቡ ከኖረበት፣ ከአገሩ፣ ከርስቱ ነው እየተፈናቀለ ያለው" የሚሉት አቶ ደጀን መንግስት ይህንን ኃይል ያደራጀው አካል በመመርመር ሥር ነቀል ለውጥ እንዲያመጣ አሳስበዋል።

በቀጣይም ኮሚቴ አዋቅረው ለኢህአዴግ ፅ/ቤት፣ ለአዴፓ ፅ/ቤትና ለጠቅላይ ሚንስትር ፅ/ቤት ኃሳባቸውን ለማቅረብ እንደተዘጋጁ ገልፀውልናል።

ምንጭ:- ቢቢሲ
@YeneTube @FikerAssefa