YeneTube
119K subscribers
31.3K photos
483 videos
79 files
3.86K links
መረጃዎችን ለመላክ @Fikerassefa
Download Telegram
ሰው በማገት 200ሺህ ብር የተቀበለው ግለሰብ ተፈረደበት!

የጣቁሣ ወረዳ ነዋሪ የሆነው ተከሳሽ አንደበት አዛናው ህዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ 1:30 በወረዳው ሮቢት አይብጋ ቀበሌ ልዩ ቦታው ደኑ እየተባለ ከሚጠራው ቦታ ላይ ነበር የወንጀል ድርጊቱን የፈፀመው፡፡

የግል ተበዳይ የሆነውን ሊቀ ጉባኤ አስካለ ካሳሁንን ከጎንደር ከተማ ወደ አለፋ ወረዳ ሻሁራ ከተማ ለስራ በመሄድ ላይ ሳለ ከመኪና በማስወረድ ጠልፎ መውሰዱን አዲስ ዘይቤ ያገኘችው መረጃ ያሳያል፡፡የወረዳው ዐቃቤ ሕግም የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ ‹‹ሰዉን መጥለፍ›› አንቀጽ 586 እና 590(2) (ሐ) ን በመጥቀስ በወረዳው ፍርድ ቤት ክስ መስርቶ ሲከራከር ቆይቷል፡፡

ተከሳሹ ተበዳዩን ከጠለፈ በኋላ 200,000 ብር መቀበሉንም አቃቤ ህግ በክሱ ያካተተ ሲሆን ይህንንም በማስረጃ አስደግፎ አቅርቧል፡፡መዝገቡን ሲመረምር የቆየው ችሎቱም በ14 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ በይኗል፡፡

[@addiszeybe]
@YeneTube @FikerAssefa
የበረሃ አንበጣ መንጋ ከሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ እየገባ መሆኑ ተገለጸ!

የግብርና ሚኒስቴር በሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ባካሄደው የመስክ ምልከታ አዲስ የተራባው የበረሃ አንበጣ መንጋ ከሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ እየገባ መሆኑን ገልጿል፡፡ወቅታዊ የአየር ሁኔታ ለመራባት ምቹ በመሆኑ በምስራቅ ኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ሰፊ እርባታ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል ነው የተባለው፡፡በግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ በላይ ንጉሴ በመራባት ላይ የሚገኝ የበረሃ አምበጣ መንጋ ከሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ እየገባ መሆኑን ከስፍራው ለዋልታ ተናግረዋል፡፡በሶማሌ ክልል፣ በምስራቅ ኦሮሚያ እና በደቡብ ክልል ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ በ13 አውሮፕላኖች የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት አቶ በላይ፣ በመኸር ሰብል ላይ ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

ፋኦ ለኬሚካል ርጭት የሚያገለግሉ አውሮፕላኖች፣ መኪኖች፣ ኬሚካሎች እንዲሁም የገንዘብ እና የባለሙያ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ የአንበጣ መንጋ መከላከል የሚቻለው አገራት በትብብር መስራት ሲችሉ በመሆኑ በምስራቅ አፍሪካ የአንበጣ መከላከል ድርጅት ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ከ35 ሚሊየን በላይ ሰዎች ከፍተኛ የምግብ እጥረት ባለባቸው ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን እና መንጋውን መቆጣጠር ካልተቻለ ተጨማሪ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎች ለከፍተኛ የምግብ እጥረት እንደምዳረጉ የፋኦ መረጃ ያመለክታል፡፡በሚቀጥሉት ወራት መንጋው ለኤርትራ፣ ለሳውዲ አረቢያ፣ ለሱዳን እና ለየመን አዲስ ስጋት እንደሚሆንም ተጠቁሟል፡፡

Via Walta
@YeneTube @FikerAssefa
ጃፓን በኤርትራ ኤምባሲ ልትከፍት ነው!

ጃፓን በኤርትራ ኤምባሲ እንድትከፍት የሀገሪቱ መንግስት ካቢኔ ወሰነ፡፡ካቢኔው ውሳኔውን ያሳለፈው የሀገራቱን ግንኙነት ለማጠናከር በማሰብ ነው፡፡ውሳኔውን በተመለከተ መግለጫ ያወጣው በጃፓን የኤርትራ ኤምባሲ ውሳኔውን መቀበሉን አስታውቋል፡፡ሁለቱ ሀገራት በማዕድን እና በሌሎችም የኢንቨስትመንት ዘርፎች ያላቸውን ግንኙነት መግለጫው ጠቅሷል፡፡ቶኪዮ እና አስመራ ግንኑነት የጀመሩት ኤርትራ በጣሊያን ቅኝ ግዛት ሥር በነበረችበት ጊዜ ነው እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፡፡ኤራትራ ከ 17 ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ በ2003 ነበር በጃፓን ኤምባሲዋን የከፈተችው፡፡ አምባሳደር እስጢፋኖስ አፍወርቂም በጃፓን የሀገሪቱ ከፍተኛ ዲፕሎማት ሆነው በአምባሳደርነት ሀገራቸውን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡

[Al-ain]
@YeneTube @FikerAssefa
“በታጠቁ ኃይሎች ላይ የመጨረሻ የሕግ ማስከበር እርምጃ እንዲወሰድ ተወስኗል” የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ኀላፊ መለስ በየነ

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ተደራጅተው በዜጎች ጥቃት የሚፈጽሙ የታጠቁ ኃይሎችን በሰላማዊ መንገድ ትጥቅ ካልፈቱ መንግሥት የመጨረሻ ሕግ የማስከበር ሥራ እርምጃ እንደሚወስድ መወሰኑን የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

@YeneTube @FikerAssefa
ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ “በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ የተደረገው የማሻሻያ ስራ (ሪፎርም) ከጉድ አድኖናል” ብለዋል!

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሀገራዊ ከመሆን ይልቅ በጎጥ የሚያስብ እንዲሆን ሲደረግ እንደነበር የጦር ኃሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ተናግረዋል፡፡

ኤታማዦር ሹሙ ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ ጋር ባደረጉት ቆይታ ፣ ሀገራዊ ሰራዊት እንዳይገነባ የሚያደርጉ አሰራሮች ነበሩ ብለዋል፡፡

“አንዳንዱ ምንም ሳይሰራ ዕውቅና የሚሰጥበት፣ አንዳንዱ ደግሞ ብዙ ሰርቶ የማይበረታታበት አሰራር ነበር” የሚሉት ኤታማዦር ሹሙ ይሁንና የመከላከያ ሰራዊት ተቋም ስለሆነ “ሁሉንም መጥፎ ነገር ተሸክሞ” ግዳጁን ሲወጣ መቆየቱን አንስተዋል፡፡

“እነዚህ ሁሉ ችግሮች እንዲፈጠሩ ያደረጉት የሰራዊቱ መሪዎች አይደሉም” ያሉም ሲሆን “እንደዚህ ያደረገው ጄኔራል ሳሞራ ነው ብዬ አልልም” ብለዋል፡፡

“ጄኔራል ሳሞራን ራሱ የሚመራው መንግስትና ፓርቲ አለው” የሚሉት ጀነራሉ “በተሰጠው አቅጣጫ ነው የሚሄደው ነው” ያሉት፡፡ ይሁንና “እሱ ይህንን ምን ያህል ይቃወም ነበር የሚለውን አላውቅም ፤ ነገር ግን አሰራሩ ትክክል እንዳልነበረ ልቦናው የሚነግረው ይመስለኛል” ብለዋል፡፡

ኢታማዦር ሹሙ “ሌሎቹ ደስ ብሏቸው” ይሰሩ እንደነበር ገልጸው የዚህ ደግሞ ምክንያቱ “አብዛኛው ከአንድ አካባቢ የመጣ” መሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ 

ሙሉውን ለማንበብ 👇👇
https://am.al-ain.com/article/it-was-an-army-that-should-have-been-dismantled-by-the-then-system-said-ethiopian-army-chief-general-berhanu-jula

@YeneTube @FikerAssefa
የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ሴት ልጅ ሰምኻል መለስ ትናንት በመቀሌ ከተማ እንደታሰረች እናቷን አዜብ መስፍንን በምንጭነት ጠቅሶ ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል። ልጃቸው ለምን እንደታሰረች ግን ምክንያቱን ገና እንዳላወቁ የተናገሩት አዜብ፣ ሰምኻል ወደ መቀሌ የሄደችው ግን የትግራዩ ግጭት ከመጀመሩ በፊት እንደሆነ ገልጸዋል። ብርሀነ መስቀል ኃየሎም የተባለው የሟቹ ጀኔራል ኃየሎም አርዓያ ልጅም እዚያው መቀሌ ውስጥ እንደታሰረ ዘገባው አክሎ ጠቁሟል።

[BBC/Wazema]
@YeneTube @FikerAssefa
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) መንግስት የድርጅቱን አመራሮች እና የፓርቲው ልሳን ሚዲያ ሙያተኞችን አስሮብኛል ሲል አማረረ፡፡

ፓርቲው ባወጣው መግለጫ "በመንግስት የፀጥታ አካላት ታፍነው ተወስደዋል" ያላቸው ስምንት የፓርቲው አመራር አባላት እና ሁለት የኦነግ ልሳን ሚዲያ (የኦሮሞ ነጻነት ድምጽ በኦሮምኛ ምእፀሩ/SBO) ሁለት ጋዜጠኞች ናቸው፡፡ገዢውን የብልጽግና ፓርቲን በዚሁ መግለጫው የከሰሰው ኦነግ ትናንት ታህሳስ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. 10 (አስሩም) አባላቶቹ በመንግስት የፀጥታ አካላት ተወስደው ለእስር መዳረጋቸውንም አብራርቷል፡፡የፓርቲው ጊዜያዊ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ እርምጃውን ብልጽግና ፓርቲ በኦነግ ላይ የከፈተው ዘመቻ አካል ብለውታል።በገዢው የብልጽግና ፓርቲ በኩል አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ቃል አቀባይ አቶ ታዬ ደንደአ ግን ክሱን በማጣጣል፤ ሂደቱን ገለልተኛ ተቋማት የህግ የበላይነትን ለማስከበር የሚወስዱት እርምጃ ነው ብለውታል፡፡

Via DW
@YeneTube @FikerAssefa
በወላይታ ሶዶ ከተማ በተከሰተው የእሳት አደጋ ዙሪያ ለተጎጂዎች ዘላቂ ድጋፍ ለመስጠት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተካሄደ!

የደቡብ ክልል የተለያዩ ቢሮ ኃላፊዎች፣ የወላይታ ዞንና የሶዶ ከተማ አመራር አካላት ትናንትና በወላይታ ሶዶ ከተማ የተከሰተው የእሳት አደጋ ያደረሰውን ጉዳት በመመልከት ቀጣይ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

አደጋው ያደረሰውን ጉዳት በመለየት ቀጣይ ዘላቂ ድጋፍ ለመሠጠት የሚያስችል ኮሚቴ ተዋቅሯል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር እንድሪያስ  በገበያው በተከሰተው አደጋ ሰለባ የሆኑ ነጋዴዎች ለረዥም ጊዜ ደክመውና ለፍተው ያፈሩት ሀብት በእንዲህ አይነት ሁኔታ ሲወድምባቸው የሚሰማቸው ሀዘን ጥልቅ መሆኑን ገልፀው የዞኑ አስተዳደርና መላው የወላይታ ህዝብ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖችን ለመደገፍ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል፡፡

ከተማዋ ከዚህ በፊት አራት ጊዜ እንዲህ አይነት ተመሳሳይ የእሳት አደጋ ማስተናገዷንና ይህም አምስተኛ ጊዜ የተከሰተ አደጋ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር እንድሪያስ ቀጣይ በአደጋው የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋምና ዘላቂ መፍትሔ ለመፍጠር አንድ አቢይና የተለያዩ ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማቋቋም ከነገ ጀምሮ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ከደቡብ ክልል የተለያዩ ቢሮዎች የመጡ ኃላፊዎችም የእሳት አደጋው ያደረሰውን ጉዳት ተዘዋውረው ከተመለከቱ በኋላ በከተማዋ በደረሰው አደጋ ማዘናቸውን ገልጸው የወላይታ ዞን አስተዳደርና እና የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር በአደጋው ምክንያት የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ ለሚያደርጉት ተግባር የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ነው የገለጹት፡፡

[FBC]
@YeneTube @FikerAssefa
"ጥቃት ሲፈጸምብን የተዋጋነው መሬት ፍለጋ ሳይሆን የተቀማነውን ማንነት ለማስመለስ ነው" አቶ አገኘሁ ተሻገር

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር የአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጅት ሠራተኞች ህግ በማስከበር ሂደቱ መረጃ በትክክልና በታማዓኒነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ መረጃ አድርሰዋል ብለዋል።

ጦርነቱ የፍትህና የመገፋት ጦርነት ነበር፤ ተገፍተንም ስለነበር ድል አድርገናል።

አሁን ዓላማ አለን በርካታ ሥራአጥ ወጣት አለን፣ የልማት ሥራ እንሰራለን።

ጦርነቱ ለችግር ደራሽነቱን፣ ጀግንነቱንም ያሳየበት ነው፣ ጋዜጠኞች መረጃ በትክክል በማድረስ ሚናቸውንም ተወጥተዋል ብለዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳደሩም በሁሉም ግምባሮች ለዘገቡ የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅትና የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን ጋዜጠኞች ሽልማት አበርክተዋል፡፡

[አብመድ]
@YeneTube @FikerAssefa
በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ እና በዙሪያው ባሉ ከተሞች ተቋርጦ የነበረውን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ወደ መደበኛ አገልግሎት አሰጣጡ ሙሉ በሙሉ ለመመለስ እየተሰራ ይገኛል ተባለ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከፍተኛ አመራሮች በትግራይ ክልል በአንዳንድ ቦታዎች በመዘዋወር የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ላይ ምልከታ አካሂደዋል፡፡በአሁኑ ወቅት ዋጃ፣ አላማጣ፣ ኮረም፣ ማይጨው፣ መሆኒ፣ ዓዲጎሱ፣ አዲ ጉደም፣ ኩሓ፣ መቐለ፣ ውቅሮ፣ አጉላዕ፣ ዓዲግራት፣ ሓውዘን እና በአፋር ክልል ስር የሚገኙ በርሃሌ እና አጉላ ከተሞችም ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡በተጨማሪም ፍረወይኒ፣ ዕዳጋ ሐሙስ፣ ዓብይ አዲ፣ ዛላንበሳ፣ ደውሃን፣ የጭላ፣ ሀገረ ሠላም እና አፅቢ በቅርብ ቀን ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ እየተሰራ ይገኛል፡፡

ሠራተኛው በክልሉ በተፈጠረው ሁኔታ በመሠረተ ልማቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰ ቢሆንም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በቅንጅት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ህብረተሰቡ የተቋረጠበትን ኤሌክትሪክ እንዲያገኝ ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ መሆኑ በአካል በተደረገ የመስክ ምልከታ ለማረጋገጥ የተቻለ ሲሆን ጉዳት የደረሰበትን መስመር መልሶ በመጠገን ወደ ስራ ለማስገባት ተቋሙ ባለ 50 ኤሲ 45ሺህ ሜትር፣ ባለ 95 ኤሲ  9 ሺህ እና ኮምፖስድ ኢንሱሌተር የተባሉ ግብዓቶች ለክልሉ እንዲደርስ የተደረገ ቢሆንም ኔትዎርኩ ላይ ከደረሰው ጉዳት አኳያ በቀጣይ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል፡፡ቡድኑ ከታህሳስ 17 እስከ ታህሳስ 12 ቀን 2013 ዓ.ም የመስክ ምልከታ ያደረገባቸው የመቀሌ፣ ኩሂያ፣ ውቅሮ፣ አጉላ፣ ፍረወይኒ፣ እዳጋሀሙስ፣ ነጃሺ፣ አዲግራት ከተሞች የሚገኙ የአገልግሎቱ ሠራተኞችና ቢሮዎችን እንዲሁም በጥገና ስራ ላይ የሚገኙ ባለሙያዎችን ጭምር በመጎብኘት ከማበረታታቱ ባሻገር ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች የለየ ሲሆን በቀጣይ ሊደረጉ የሚገባቸው ድጋፎችንም ለይቷል፡፡

በመጨረሻም ስለ ነባራዊ ሁኔታና ቀጣይ አቅጣጫ ዙሪያ በመቀሌ ሪጅን ኤሌክትሪክ አገልግሎት በመገኘት ከማኔጅመንቱ ጋር የምክክር መድረክ በማድረግ ጉብኝቱን አጠናቋል፡፡
የህብረተሰቡን ኃይል ፍላጎት በአፋጣኝ ወደ ቀድሞው አገልግሎት ለመመለስ ሲሰሩ የቆዩ የትግራይ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጥገና ክፍል ሰራተኛች የማኔጅመንት አባላት አድንቀዋል፡፡ተቋሙ በክልሉ ጉዳት የደረሰባቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማቶች ጠግኖ ሁሉንም የክልሉ ከተሞች እና የገጠር ቀበሌዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ኃይል እንዲያገኙ ለማድረግ እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡
 
Via EEU
@YeneTube @FikerAssefa
የሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የወጪ ንግድ ገቢ በ11 በመቶ ቀነሰ!

የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከውጪ ንግድ ያገኘው ገቢ ከባለፈው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ11 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱ ተገለጸ።የኢንስቲትዩቱ የውጪ ንግድ አፈጻጸም በበጀት ዓመቱ በመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከንዑስ ዘርፉ ምርቶች የወጪ ንግድ 27 ነጥብ 41 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 17 ነጥብ 25 ሚሊዮን ዶላር ወይም የዕቅዱ 62 በመቶ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲቱዩት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ደበሌ ለማ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ይህም የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃፀም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 19 ነጥብ 52 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ጋር ሲነፃፀር የ2 ነጥብ 27 ሚሊዮን ዶላር ወይም 11 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ገልጸዋል።

ለዕቅድ አፈፃፀም ማነስ ምክንያት የአጠቃላይ የዕቅዱን 18 በመቶ ድርሻ የነበራቸዉ ኹለት ኤክስፖርት ቄራዎች (አክሸከርና ሔልሜክስ) እና ስድስት የእርድ ተረፈ ምርት ላኪዎች (ዮንግታይ፣ ኪንግ ድራጎን፣ በላይነህ፣ ደመቀ አክሊሉ፣ ጉተማ ጉታ፣ ኃይሉ ፈዬ) በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ምንም ምርት አለመላካቸዉ እና በጥራት እና በዋጋ ተወዳዳሪ ሆኖ ከመቅረብ ጋር በተያያዘ በዓለም ደረጃ እያደገ በመጣው ውድድር እንዲሁም የአገር ውስጥ የማር ዋጋ እየጨመረ በመምጣቱ በዕቅዱ ታሳቢ ከተደረጉት የማር እና ሰም አቀነባባሪ(ላኪዎች) ምንም ምርት አለመላካቸው በዕቅድ አፈፃፀም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል ተብሏል።

Via Addis Maleda
@YeneTube @FikerAssefa
የታሪክ ምሁራንና የታሪክ ፀሐፊያን የሚሳተፉበት የውይይት መድረክ ለማካሄድ ዝግጅት መጠናቀቁን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ከ60 በላይ የኢትዮጵያ የታሪክ ምሁራንና የታሪክ ፀሐፊያን ይሳተፉበታል፡፡መድረኩን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ፣ ዴስቲኒ ኢትዮጵያና ሀሴት የሳይኮ ቴራፒ ማዕከል አስተባብሩታል፡፡

በሰላም ሚኒስቴር አስተባባሪነት እየተካሄደ ለሚገኘው የብሔራዊ የማህበረሰብ ተኮር የምክከር መድረክ አንዱ አካል ነው፡፡

ምሁራኑና የታሪክ ፀሐፊያኑ የተመረጡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ አማካኝነት ሲሆን ተወያዮች በነፃነት ሃሳባቸውን የሚያንሸራሽበት መድረክ እንደሚሆን የሰላም ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

[ኢ.ፕ.ድ]
@YeneTube @FikerAssefa
በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ክስ ያቀረበበት ተከሳሽ በጽኑ እስራት ተቀጣ!

በአራዳ ከፍል ከተማ አካባቢ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የፈጸመው የ42 ዓመት እድሜ ያለው ተከሳሽ ሳሙኤል ሽፈራው ዐቃቤ ሕግ በመሰረተው ክስ በጽኑ እስራት ተቀጣ፡፡

የክስ መዝገቡ እንደሚያስረዳው ተከሳሽ እድሜዋ 14 አመት የሆናትን ህጻን የግብረ ስጋ ግንኙነት ለመፈጸም በማሰብ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ቦታው ካቴደራል ት/ቤት አካባቢ የግል ተበዳይን ወደ መኖሪያ ቤቱ ውስጥ በመውሰድ በተለያየ ቀን በተደጋጋሚ ጊዜ የግብር ስጋ ግንኙነት በመፈጸም የ32 ሳምንት ከ6 ቀን እርግዝና እንዲፈጠር ያደረገ በመሆኑ እና እድሜያቸው 14 አመት በሆነ እንዲሁም 18 አመት ባልሞላቸው ልጆች ላይ የሚፈጸም የግብረ ስጋ ድፍረት በደል ወንጀል በመፈጸሙ በዐቃቤ ሕግ ተከሶ ፍርድ ቤት ቀርቧል፡፡

ተከሳሽ በተከሰሰበት የወንጀል ሕግ አንቀጽ 626/1/ እና 628 /ሀ/ ስር ተከላከል ቢባልም መከላከል ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን በመመርመር ተከሳሽን ጥፋተኛ ብሎታል፡፡በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 7ኛ ወንጀል ችሎት ተከሳሽ ከአሁን በፊት ሪከርድ የለሌበትና የቤተስብ አስተዳዳሪ በመሆኑ 2 ማቅለያዎችን በመያዝ በ10 ዓመት ከ10 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡

[FDRE AG]
@YeneTube @FikerAssefa
1100 ኢትዮጵያውያን በታንዛኒያ እስር ቤቶች መታሰራቸውን በዳሬሰላም የኢትዮጵያ ኤምባሲ አረጋግጧል!

ኤምባሲው ባለፉት 3 ሳምንታት ውስጥ በታንዛኒያ 4 ግዛቶች ውስጥ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ባደረገው ጉብኝት ቁጥራቸው 1100 የሆኑ ኢትዮጵያውያን ታስረው አግኝቷል።ታሳሪዎቹ አብዛኞቻቸው ባለፉት 4 ወራት ውስጥ የታንዛኒያን ድንበር በህገወጥ መልኩ አቋርጠው በመግባታቸው በፖሊስ ተይዘው ከ6 ወር እስከ 2 አመት የሚደርስ የእስራት ፍርድ የተፈረደባቸው ሲሆኑ፤ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ከሀድያ እና ከምባታ ዞኖች የተነሱ ወጣቶች ናቸው።

በሁለተኛ ደረጃ የወላይታ እና ሃላባ ዞኖችም ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ዜጎች ታስረዋል።በጾታ ሁሉም ወንዶች ሲሆኑ እድሚያቸው ከ14 እስከ 46 አመት ባለው ውስጥ ነው።

ከታሳሪዎቹ ጋር በተደረገው ውይይት በደረሰባቸው ስቃይ እና እንግልት ክፉኛ የተጎዱ መሆናቸውን ኤምባሲው የተመለከተ ሲሆን፤ አብረዋቸው ጉዞ ጀምረው በርካቶች በመንገድ ላይ ከአጠገባቸው በሞት የተለዩ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

በአሁኑ ወቅት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት አገራት የድንበር ቁጥጥራቸውን አላልተዋል በሚል የደላሎች ማታለያ ተታለው ለስደት የተዳረጉ መሆኑን ያጫወቱ ታሳሪዎቹ፤ ሽማግሌዎች እና የሀይማኖት ተቋማት እና የቤተ እምነት አባቶች ሳይቀሩ ጸሎት እና ምርቃት በማድረግ አበረታትተው በመሸኘት ላይ መሆናቸውን ከታሳሪዎቹ አንደበት ለመስማት ተችሏል።

ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ ኤምባሲው ከ3100 በላይ ዜጎችን ከእስር አስፈትቶ ወደ አገር ቤት መመለሱ ይታወሳል።

ህገወጥ ስደትን ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካላት (የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ) ሃላፊነታቸውን በአግባቡ የመይወጡ ከሆነ የዜጎችን ስቃይ እና እንግልት እንዲሁም ሞት ማስቆም አይቻልም፤ የአገራችንን መልካም ገጽታም በከፍተኛ ደረጃ የሚያጎድፍ ተግባር ነው።

[በዳሬሰላም የኢትዮጵያ ኤምባሲ]
@YeneTube @FikerAssefa
ሀዋሳ ከተማን ለማስዋብ 60 ሚሊዮን ብር ተበጀተ!

በሀዋሳ ከተማ በተለምዶ ጥቁር ውሃ ከሚባለው ቦታ አንስቶ አስከ ሞኖፖል ድረስ 7.5 ኪ.ሜ የሚሸፍን ቦታን የማስዋብ ስራ ሊሰራ መሆኑን የከተማ መስተዳደሩ ገልጿል፡፡ይህ የማስዋብ ፕሮጀክት በሶስት ዓመታት እንዲጠናቀቅ ዕቅድ የተያዘለት ሲሆን ግንባታውን የሚያከናውኑ ተቋራጮችን ለማወዳደር ግልፅ ጨረታ ይወጣል ተብሏል፡፡

ሙሉ በሙሉ በከተማው መስተዳደር ወጪ የሚገነባው ይህ የማስዋብ ስራ በጥቅሉ 60 ሚሊዮን ብር በጀት የተያዘለት ሲሆን ከዚህ ውስጥ 20 ሚሊዮኑን ከተያዘው በጀት ዓመት እንደፀደቀ በመስተዳደሩ የመሰረተ ልማት እና እቅድ ቢሮ የበጀት ሲቪክ እና ትብብር ሀብት አስተዳደር ዘርፍ እና ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ተአምር ቶማስ ለአዲስ ዘይቤ ገልጿል፡፡

በርካታ መዝናኛዎችን የሚያጠቃልለው ይህ የማስዋቢያ ፕሮጀክት የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ዋናው ግቢ አከባቢ አስተዳደራዊ አከባቢዎች፣ የልጆች መጫወቻዎች እና መዋያ ቦታዎች እንዲሁም ሁለገብ እንቅስቃሴ የሚደረግባቸው ስፍራዎች የፕሮጀክቱ ዋና ዋና አካሎች እንደሆኑ የአስተዳደር ህዝብ ግንኙነት ቢሮ አስረድቷል።

[@addiszeybe]
@YeneTube @FikerAssefa
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ልጅ ሰምሃል መለቀቋን እናቷ አዜብ መስፍን ገለጹ!

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ልጅ ሰምሃል መለስ ትግራይ ውስጥ በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ከቆየች በኋላ መለቀቋን እናቷ ወይዘሮ አዜብ መሰፍን ለቢቢሲ ገለጹ።

ወ/ሮ አዜብ እንዳሉት ሰምሃል ከእሁድ ጀምሮ አስከ ሰኞ ምሽት ድረስ ለ36 ሰዓታት ተይዛ መቆየቷን ገልጸው፤ ትናንት ምሽት እራሷ ደውላ መለቀቋን እንደገለጸችላቸው ለቢቢሲ ዛሬ [ማክሰኞ] ጠዋት ተናግረዋል።

@YeneTube @FikerAssefa
100 የዲያሊስስ ማሽኖች ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ ነው!

በያዝነው ዓመት ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢዎች ጋር በመሆን 100 ለኩላሊት ዕጥበት ወይንም ዲያሊስስ ሕክምና የሚያገለግሉ ማሽኖች ወደ አገር ውስጥ እንደሚያስገባ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢዎች ኤጀንሲ ጋር በመሆን እቅድ ይዞ በዚህ የበጀት ዓመት 100 ያህል የኩላሊት ዕጥበት ሕክምና ለመስጠት የሚያስፈልጉ ማሽኖችን ለማስገባት እየሠራ እንደሆነ አባስ ሃሰን የጤና ሚንስቴር የክሊኒካል አገልግሎት ዳይሬክተር ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

@YeneTube @FikerAssefa
ም/ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ሱዳን ገቡ!

የኢትዮጵያ እና የሱዳን የጋራ የድንበር ኮሚቴ ውይይት ላይ ለመታደም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ዛሬ ሱዳን ካርቱም ገብቷል፡፡የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር ቀንዓ ያደታ (ዶ/ር) እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ ገዱ አንዳርጋቸውም በጉብኝቱ ተካተዋል፡፡

[Al-ain]
@YeneTube @FikerAssefa
ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ የትምህርት ሚኒስቴር አሳሰበ።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝን በመከላከል የመማር ማስተማር ስራው ቢጀመርም በርካታ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘት አልቻሉም ተብሏል።በዚህ ጉዳይ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር አመራሮችና የክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች በበይነ መረብ መክረዋል።ተቋርጦ የነበረው የመማር ማስተማር ስራ ድጋሚ የተጀመረ ሲሆን አሁንም ወደ ትምህርት ገበታቸው ያልተመለሱ ተማሪዎች እንዳሉ ተነስቷል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ፒ ኤች ዲ) ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ አሳስበዋል።ትምህርት ላይ የሚሰሩ አጋር አካላትና ከትምህርት ዘርፍ ውጭ ያሉ ተቋማትም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ያለውን ጥረት እንዲደግፉ ጠይቀዋል።"ወደ ትምህርት ቤት እንመለስ" በሚል ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው የመመለስ ዘመቻም ይጀመራል።

[MoE]
@YeneTube @FikerAssefa
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞን ነዋሪዎች ጋር ተወያዩ።

በውይይት መድረኩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኤታማጆር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ እና ሌሎች የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

በመድረኩ ላይ በአካባቢው የተከሰተውን የፀጥታ ችግር መፍታት በሚቻልበት አግባብ ላይ ውይይት ተካሄዷል።

[FBC]
@YeneTube @FikerAssefa