ዐውደ ምሕረት
3.69K subscribers
930 photos
24 videos
271 files
193 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
#በሁለት_ዝሆኞች ትግል የሚጎዳው ሳሩ ነው !
____________________________

በጥንት ጊዜ ሁለት ውርዘው ነጌ የሆኑ ሁለት ዝሆኖች ክፉኛ ይጋጩና በጨበጣ ውጊያ በክርኖቻቸው፣በግንባሮቻቸው ይጋጩ ፣በረጃጅም ኩምቢዎቻቸውም ይናረቱ ጀመር። ጠቡ እየከረረ ሄዶ ምድር ስትጨነቅ ከበላያቸው እጅግ ብዙ ጆፌ አሞሮች የተጣለ ግዳይ ለመዘንጠል ማንዣበብ ጀመሩ ። ይኸኔ የአሞሮቹን ማንዣበብ ያጤነው አንደኛው ዝሆን ጠቡን አስታግሶ
#ስማኝማ_አንዴ እነዚህ አሞሮች ምን ነክቷቸው ነው ከበላያችን በማንዣበብ የሚዞሩን ?" ሲል ሌላኛውን ዝሆን ይጠይቃል።
#ተጠያቂው ዝሆንም "እነዚህ አሞሮች የሚከታተሉት የእኛን ድብድብ ሲሆን የሚጠብቁትም የእኛን ሞት ነው። ከሁለት አንዳችን ወይም ሁለታችንም ስንሞት ይወርዱና ይቦጫጭቁንና ይበሉናል።" አለው።

የመጀመሪያ ጠያቂ ዝሆንም ቀበል አድርጎ "እንዲህ ከሆነ ታዲያ እኛ መጣላታችንን ለምን አንተወውም?"ሲል ሌላኛው ውርዝው ዝሆን በአሳቡ ተስማምቶ ሁለቱም ጠባቸውን ትተው በፍቅር ተነስተው ተያይዘው ሄዱ። ያንዣብቡ የነበሩ ጆፌ አሞሮችም የሚቦጫጭቁትና የሚዘነጣጥሉት ግዳይ ስላጡ አዝነው ተበታተኑ ይባላል።

#ዘንድሮ ግን አሞራዎቹ የኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ሳይገናኙ አይቀሩም የወንድማማቾች ጠብ የግዳይ ብፌን ከምድሪቱ አዘጋጅቶ ብሉልኝ ጠጡልኝ ሲል ጋብዟቸዋልና ጠሪ አክባሪ ብለው ይመጣሉ አይቀሩም ። ለዛውም ነጭ ጆፌ አሞሮች ! ልዮነትን በልባቸው ይዘው የጋራ የሠላም መንገድን በአንድ መጓዝ እንደሚቻል ከዝሆኖቹ አልተማሩምና ዝሆኖቹ ጠቡን አቁመው በሠላም መጓዝ የቻሉት ያጋጫቸው ነገር ተፈቶላቸው ላይ ሆን ይችላል በእርስ በእርስ ፍጭት ግን ተጠቃሚው አካል ሌላ መሆኑን ስለተገነዘቡ ግን በልዮ ነት ውስጥ አንድነትን መሠረቱ። ዝሆኖች እርስ በእርስ ሲጣሉ ወይም ሲታገሉ ከርመው ሳይጎዳዱ ሊለያዮ ይችላሉ ነገር ግን እነርሱ የተጣሉበት የሳር ምድር ወደፊት ምድረ በዳ ሊሆን ይችላል ። ለዛ ነው ብዙ ጊዜ በዝሆኖች ጠብ ወይም ትግል ተጎጂዎቹ ሳሮች ናቸው የሚባለው። ዛሬም በዝሆኖች ትግል እየታሸች ያለችሁ መከረኛዋ ቤተ ክርስቲያን ነችና ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ያሻታል!

በቀኝ ግዛት ይዘው ይግጡን ዘንድ ባይቻላቸው በእጅ አዙር በዘመናዊነት ሰበብ በሃይማኖት፣በፖለቲካ ፣በብሔር፣ እንድንበታተን Timer Explosive /በሰዓት የተጠመደ ፈንጂ/ በሕሊና ና በልቡናችን አጠመዱብን፤ ፈንጂውም እነሆ ጊዜውን ጠብቆ መፈንዳቱን ቀጠለ። የተበተነ መንጋ ለአዳኝ ምቹ ነውና አንበሳ እንዳገኘው ከመንጋው እንደተለየ የሜዳ አህያ ሰብሕናና ሞራላችንን ሰባብረው፣ ገነጣጥለው ሊበሉን በዙሪያችን አደቡ ።

#ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ እንደ ኖኅ እራሳችን የተከልነውን ሀገር በቀል በሆኑ ዕውቀቶች መመርመርና ጥንታዊ የሆኑ የአባቶቻችንን የጥበብ ወይን ጠጅ መጎንጨት አለ መፈለጋችን ነው። ከዚህ ይልቅ ከምዕራባውያን የተንኮል ጋን መናኛውን የወይን ጠጅ ጠጥተን እንጠግብ ዘንድ ተመኘን በመንፈሰ ስካርም የእናት ልጅ ወንድምን ገለን ዳኪራ መርገጥን አመጣን ካም የሆነች ዓለምም ኃፍረታችንን እያየች ሳቀችብን !
በወንድማማቾች ጠብ ሟችና ተቅበዝባዥ እንጂ ጀግና የለም! በመሆኑም በወንድሞቻችን ጥፋት እናዝናለን እንጂ ጮቤ አንረግጥም ።ሆኖም ግን ትናንታችንን መርሳት እንደሌለብን በእጅጉ አስተምረውናል ወደ ሥልጣን የመጡበትን ቀን እንደ አቡነ አረጋዊ በዓል ጠላ እየጠመቅን እናክብር እዳላሉ ዛሬ ስም አጣራራቸውም ሳይቀር ጠፍቷል ። ሃያ ሰባት ዓመት የታገሰ እግዚአብሔር ጫካ ነበርሽና ወደ ጫካም ተመለሺ ብሎ በ27ቀን ማዋረድም ይችላል።
#እግዚአብሔር ግን ሁል ጊዜም ይህችን ሀገር የአባታቸውን ኃፍረት ላለማየት ወደ ዋላቸው ሄደው የአባታቸውን እርቃን የሸፈኑ ሴምና ያፊትን የመሰሉ ቡሩካንን አያሳጣትምና ይህው ዛሬም በቸርነቱ ከነ ነፃነታችን ሳንሸማቀቅ አለን።
የፍቅርን፣የይቅር ባይነትን፣የአክብሮትን ጋቢ ይዘው ወደ ዋላ ታሪካቸው ሄድ ብለው አባት ሀገራቸው ከመውደቁ በፊት የነበረውን ክብርና ልዕልና የሚረዱና ወደ ፊትም በልዕልና ሊነሳ እንደሚችል ጭምር ተገንዝበው ብድራታቸውን በምረቃቱ ከነ ትርፉሁ ሊሰጣቸው እንደሚችልም አምነው የሀገርን አፍረት የሚሸፍኑ ሴም እና ያፌቶች ልንሆን ይገባል ። 🙏


የመነሻ ወግ ምጥን ቅመም /በመ/ር ምትኩ አበራ/

ተክለ ኤል ኃ/ማርያም
አ.አ ኢትዮጵያ
ኅዳር 20/2013ዓ.ም