ስንክሳር
7.32K subscribers
825 photos
4 videos
37 files
237 links
በስንክሳር channal ስንክሳሩ ተገልጦ ቅዱሳን ይዘከራሉ፣ ወቅቱን የጠበቁ መረጃዎችን ያገኛሉ፡፡ ይከታተሉን!
Download Telegram
እንኩዋን ለእመቤታችን
#ቅድስት_ድንግል_ማርያም ዓመታዊ የጽንሰት በዓል
በሰላም አደረሳችሁ
ቁጽረታ ( #ጽንሰታ ) ለማርያም
ይህችን ዕለት አበው ሊቃውንት "ጥንተ
መድኃኒት_የድኅነት መነሻ ቀን" ሲሉ ይጠሯታል:: ስለ ምን
ነው ቢሉ:- ለዓለም ድኅነት ምክንያት የሆነች የአምላክ እናቱ
የተጸነሰችበት ዕለት በመሆኑ ነው:: አንድም ከአዳም ስሕተት
በሁዋላ ያለ ጥንተ አብሶ የተጸነሰች የመጀመሪያ ሰው እርሷ
ናትና እንዲህ ይላሉ::
"ለጽንሰትኪ በከርሥ: እንበለ አበሳ ወርኩስ: ወለልደትኪ
እማሕጸን ቅዱስ::"
" #ድንግል_ሆይ ! መጸነስሽ ያለ በደል (ያለ ጥፋት) ነው:
የተወለድሽበት ማሕጸንም ቅዱስ
ነው::" ( መጽሐፈ_ሰዓታት , ኢሳ. 1:9, መኃ. 4)
ይሕች ዕለት ለኢያቄምና ለሐና ብቻ ሳይሆን ለፍጥረት ሁሉ
የተስፋ ድኅነት ቀን ናትና ሐሴትን ልናደርግ ይገባል::
የእመቤታችን መጸነስስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
ከነገደ #ይሁዳ የሚወለድ #ቅዱስ_ኢያቄም የሚባል ደግ
ሰው ከነገደ #ሌዊ ( #አሮን ) የተወለደች #ሐና የምትባል ደግ
ሴት አግብቶ: በሕጉ ጸንተው: በሥርዓቱ ተጠብቀው ይኖሩ
ነበር:: ነገር ግን በዘመኑ ሰዎች "ልጅ የላችሁም" በሚል
ይናቁ ነበር::
ኦሪታውያን ልጅ የሌለውን "ኅጡአ በረከት-ከጸጋ
#እግዚአብሔር የራቀ" ነው ብለው ያምኑ ነበር:: ኢያቄምና
ሐና ልጅ እንዲሰጣቸው ሲያዝኑ: ሲጸልዩ ዘመናቸው አልፎ
አረጁ:: እነሱ ግን የሚያመልኩት #የአብርሃምና_ሣራን
አምላክ ነውና ተስፋ አልቆረጡም::
የለመኑትን የማይነሳ ጌታ በስተእርጅናቸው ድንቅ ነገርን
አደረገላቸው:: አንድ ቀን እርግቦች ከጫጩቶቻቸው ጋር
ሲጫወቱ የተመለከተች #ቅድስት_ሐና ፈጽማ አለቀሰች::
"እንስሳትና አራዊትን: እጽዋትን በተፈጥሯቸው እንዲያፈሩ
የምታደርግ አምላክ ምነው ሐናን ድንጋይ አድርገህ
ፈጥረሃታልን?" ብላ አዘነች::
ይህን የተመለከተ ቅዱስ ኢያቄም ወደ ተራራ ወጥቶ ሱባኤ
ያዘ:: ለ40 ቀናትም ሲጸልይና ሲማለል ቆየ:: በ40ኛው ቀን
2ቱም ሕልምን ያልማሉ:: እርሱ:- #ነጭ_ርግብ ሰማያትን
ሰንጥቃ ወርዳ: በሐና ቀኝ ጀሮ ገብታ: በማሕጸኗ ስትደርስ
አየ::እርሷ ደግሞ:- የኢያቄም በትር አብቦ: አፍርቶ: ጣፋጭ
ፍሬውን ሰው ሁሉ ሲመገበው ታያለች:: ቅዱስ ኢያቄም
ከሱባኤ እንደ ተመለሰ ያዩትን ተጨዋውተው "ፈቃደ
እግዚአብሔር ይሁን" አሉ:: ለ7 ቀናትም በጋራ
እግዚአብሔርን ሲለምኑ ሰነበቱ::
በ7ኛው ቀን (ማለትም ነሐሴ 7)
#መልአከ_ብሥራት_ቅዱስ_ገብርኤል ክንፉን እያማታ ወደ
እነርሱ ወረደ:: "ዓለም የሚድንባት: የፍጥረት ሁሉ መመኪያ
የሆነች ልጅ ትወልዳላችሁ" ብሏቸው ተሠወራቸው::
እነርሱም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ::
እንደ ሥርዓቱም በዚህች ቀን አብረው አድረው
#እመ_ብርሃን ተጸነሰች::
" #ኦ_ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ
¤ድንግል ሆይ! ኃጢአት ባለበት ሥጋዊ ፍትወት የተጸነስሽ
አይደለም" እንዳለ ሊቁ:: ( #ቅዳሴ_ማርያም )
#ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ
ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል:: #ቅዱስ_ሉቃስ የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል:: "ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: (ሉቃ. 1:6)
የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል! እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር::
እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90 የዘካርያስ 100 ደግሞ ደርሶ ነበር:: ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ: ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ #መልአከ_ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው::
ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ:: ቅድስቲቷ ግን መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች:: በ6ኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ
#የአርያም_ንግሥት ድንግል እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ #ኤልሳቤጥ መጣች:: ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው::
የአምላክ እናቱ ስትደርስና "ሰላም" ስትላቸው
#መንፈስ_ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና: ዮሐንስ ደግሞ ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ):: ከዚህ በሁዋላ ሰኔ 30 ተወልዶ: አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል::
የእመቤታችን ልመናዋ: ክብሯ: የልጇ የወዳጇም ቸርነት በእውነት ከሁላችን ጋር ይሁን:: የመጥምቁንም በረከት ያብዛልን::