ስንክሳር
7.32K subscribers
825 photos
4 videos
37 files
237 links
በስንክሳር channal ስንክሳሩ ተገልጦ ቅዱሳን ይዘከራሉ፣ ወቅቱን የጠበቁ መረጃዎችን ያገኛሉ፡፡ ይከታተሉን!
Download Telegram
እንኩዋን ለታላቁ #ጻድቅና_ገዳማዊ #አባ_ዓቢየ_እግዚእ ዓመታዊ የተአምር በዓል በሰላም አደረሳችሁ
ጻድቅና #ገዳማዊ_አባ_ዓቢየ_እግዚእ
ጐንደር ከተማ ነዋሪ ከሆኑ ወይም ከተማዋን የሚያውቁዋት ከሆነ አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎ::
¤ከተማዋ ውስጥ ጅብና እባብን የመሠሉ አራዊት ነዋሪውን
ሲገድሉ ወይም ሲያቆስሉ ተመልክተው: ካልሆነም በታሪክ
ሰምተው ያውቃሉ?
¤መቸም መልስዎ "በጭራሽ አላውቅም" እንደሚሆን
እገምታለሁ:: "ግን ለምን?" ካሉ ነገሬን እንዲረዱኝ ሌሎች
የሃገራችን ዋና ዋና ከተሞችን ልብ ይበሉልኝ:: እንኩዋን
በሌሊት በቀንም አራዊቱ አይጠፉባቸውም::
¤ታዲያ ጐንደር ከተማ ውስጥ ጅብ የማይገባው: እባብና
ጊንጥ ሰው የማይገድለው በጻድቁ በአባ ዓቢየ እግዚእ ቃል
ኪዳን ምክንያት ነው:: (ሁሉም የሃገራችን ከተሞች የተባረኩ
መሆናቸውን ሳንዘነጋ ማለት ነው:: )
☞ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
አባ ዓቢየ እግዚእ የተወለዱት በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን
#ትግራይ ተንቤን ( #መረታ) ውስጥ ነው:: የተባረኩ
ወላጆቻቸው #ያፍቅረነ_እግዚእ እና # ጽርሐ_ቅድሳት
ይባላሉ:: አጥምቀው "#ዓቢየ_እግዚእ " ሲሉ ስም
ያወጡላቸው የወቅቱ ዻዻስ #ሰላማ_መተርጉመ_መጻሕፍት
ናቸው:: ትርጉሙም 'በጌታ ዘንድ ታላቅ ሰው' ማለት ነው::
ዓቢየ እግዚእ በሕጻንነታቸው ሌሊት ሌሊት ባሕር ውስጥ
ሰጥመው ሲጸልዩ አድረው ቀን ቀን እየተማሩ ብሉይ ከሐዲስ
ጠነቀቁ:: ገና በወጣትነታቸው ወደ ታላቁ መነኮስ # አቡነ_መድኃኒነ_እግዚእ (ደብረ_በንኮል) ሔደው መንኩሰዋል:: በገዳሙ በጾም: በጸሎትና በስግደት ተወስነው ከኖሩ በሁዋላ ወደ #ዋልድባ ሔደው የተሰወረች ቤተ ክርስቲያን
አግኝተዋል:: በጊዜው በ40 ቀን አንዲት ቅጠል ብቻ
ለቁመተ ሥጋ ይበሉ ነበር::
ከዚያም ወደ ሃገራቸው ተንቤን ተመልሰው ዛሬም ድረስ
ድንቅ ሆኖ የሚታየውን ገዳም መሥርተው ብዙ መናንያንን
አፍርተዋል:: ዓቢየ እግዚእ ገዳማዊና ጻድቅ ብቻ ሳይሆን
#ሐዋርያዊ አባትም ነበሩ:: ከትግራይ እስከ #ደንቢያ ደግሞ
ሃገረ ስብከታቸው ነው::
አንድ ጊዜ ደቀ መዛሙርትን አስከትለው ለስብከት
ሲንቀሳቀሱ #ተከዜ ወንዝ አካባቢ ደረሱ:: ቀኑ ነሐሴ 10
ነውና ተከዜ እስከ ገደፉ ሞልቶ ለ3 ቀናት ባለመጉደሉ
ከ1,000 በላይ ሰዎች ሲያለቅሱ ደረሱ:: ጻድቁ ባካባቢው
የነበሩት ኢ-አማንያን (አሕዛብ) ቢሆኑም ራርተዋልና
"አምላከ_ሙሴ" ብለው ጸልየው ወደ ጥልቁ ውስጥ ገቡ::
#ቅዱስ_ሚካኤል አብሯቸው ነበርና ተከዜ ግራና ቀኝ
ተከፍሎ መሃሉ የብስ ሆነ:: ይሕን ድንቅ ያዩ ከ940 በላይ
አሕዛብም አምነው በጻድቁ እጅ ተጠምቀዋል:: ይሕም
ዘወትር ነሐሴ 10 ቀን በቤተ ክርስቲያናቸው (ጐንደር)
ይከበራል::
+ከዚያም እያስተማሩ ጐንደር ደረሱ:: ያኔ ጐንደር በቀሃና
አንገረብ ወንዞች የታጠረች አንዲት መንደር ነበረች:: ጻድቁ
ቀን ቀን እየሰበኩ ማታ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናቸው የታነጸበት
ሥፍራ ላይ ሲጸልዩ ያድሩ ነበር::
+በዚያ ዘመን ጐንደር ውስጥ ጅብ: እባብና መሠል አራዊት
ገብተው ሕዝቡን ጨረሱት:: ይሕንን የተመለከቱት አባ ዓቢየ
እግዚእ ወደ እግዚአብሔር አለቀሱ:: በፍጹም ልባቸውም ስለ
ሕዝቡ ለመኑ::
የለመኑትን የማይነሳ ጌታ ወደ ጻድቁ ቀርቦ "በስምሕ
የተማጸኑ: በቃል ኪዳንህ ያመኑ: በምድር አራዊት
አይሠለጥኑባቸውም:: በሰማይም እሳትን አያዩም::
ጐንደርንም አራዊት ገብተው ሰውን አይጐዱም::" ብሏቸው
አርጉዋል:: ጻድቁም የወንጌል አገልግሎታቸውን ፈጽመው ወደ
ገዳማቸው #ተንቤን ተመልሰዋል:: ይሔው እኛ ምን
ብንከፋ: ጻድቁንም ብንረሳቸው #እግዚአብሔር ግን ዛሬም
በጻድቁ ምልጃ ከተማዋን ጠብቆ ይኖራል:: ነገን ደግሞ እርሱ
ያውቃል:: ዛሬ ቤተ ክርስቲያኑ የታነጸበት ቦታ ( #ጎንደር ቀበሌ
09 #ኪዳነ_ምሕረት ) ጻድቁ የጸለዩበት ቦታ ነው:: እንኩዋን
በወርሃዊ በዓላቸው (በ19) ይቅርና በዓመታዊ በዓላቸው
(ግንቦት 19, ነሐሴ 10) እንኩዋ ለንግስ የሚመጣው ሰው
ቁጥር ያስተዛዝባል::
አባ ዓቢየ እግዚእ በገዳማቸው ተንቤን ለብዙ ዘመናት
በቅድስና ኑረው: 3 ሙታንን አስነስተው: ብዙ ድውያንን
ፈውሰው: #ብሔረ_ብጹዓንን ጎብኝተው: የድኅነት ቃል
ኪዳንም ተቀብለው: በ140 ዓመታቸው ግንቦት 19 ቀን
አርፈዋል:: የጻድቁ ክብር ለሁሉ ነውና እናስባቸው::
ይህች ዕለት ባሕረ ተከዜን ከፍለው ሕዝቡን ያሻገሩባት:
አሕዛብንም ያጠመቁባት ናትና በገዳማቸው: ጐንደር ውስጥ
በሚገኘው ቤተ ክርስቲያናቸውም ይከበራል::
¤በረከታቸው ይደርብን::
#የዋልድባ ጉዞ ማስታወሻ- ክፍል አራት
(ወንድወሰን ውቤ)
.....ጌታችን ሆይ እስራኤልን እኮ በኪደተ እግርህ ረግጠኻታል፡፡ ዓለምን ያዳንክበትን ፍቅር በመስቀል ገልጸህባታል፡፡ ታዲያ ይህች ምድር እንዴት ዳግማዊት ኢየሩሳሌም ትሆን ዘንድ ይቻላታል? ጌታም የአንዳቸውን ከወይራ የተሠራ መቁጠሪያ ወስዶ መሬት ላይ ጣለ፡፡ ዕለቱን በቅላ ዛፍ ሆነች፡፡ መከራውን የተቀበለባት መስቀልም ከእርሷ ወጣ፡፡ ተመስጦ ሰጣቸውና በራእይ ዳግም በአይሁድ ካህናት እጅ ሲንገላታ፣ ሕማማተ መስቀልን ሲቀበል፣ ነፍሱን በፈቃዱ ሲሰጥና በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ ሲነሣ ዐሳያቸው፡፡ 
መከራውን እንደ እናቱ እመቤታች ድንግል ማርያምና እንደ ፍቁረ-እግዚእ ዮሐንስ ከልብ በሚፈልቅ እንባ ተካፈሉ፤ ድሉንም ከልብ በተቀዳ ሀሴት አጣጣሙ፡፡ አሁን ዐይነ-ሥጋቸው ደክሞ የነፍሳቸው ዐይን በደንብ በራ፡፡ አሁን እምቢታቸው ጠፍቶ ታዛዥነት ነገሠባቸው፡፡ ሰው ክርስቶስ እንዲሁ የከፈለለትን የፍቅር ዋጋ ሲረዳ የደምና የሥጋ ስሌትን አቀዝቅዞ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ አንተ ታውቃለህ ማለት ይጀምራል፡፡ እነሱም “ጌታ ሆይ እንዳልክ ይሁን የባረክልንን ዳጋማዊት ኢየሩሳሌምን ተቀብለናል፡፡ የተጠመክበት ዮርዳኖስ፣ የተንገላታህበት ጎልጎታ፣ የተሰቀልክበት ቀራንዮ አለንና በዚህ መሆን ለኛ መልካም ነው፡፡” አሉ፡፡ 
እንግዲህ ዋልድባ ገዳም ጌታ ራሱ ባርኮ የገደመው ቅዱስ ቦታ መሆኑ ነው ታላቅነቱ፡፡ አስቀድሞም በሕጻንነቱ እመቤታችን ይዛው በተሰደደች ጊዜ በዚህ ቦታ ዐርፈው ነበርና ያኔ እንደባረካት ይነገራል፡፡ ባርኮ አጸናቸው፣ ለምንኩስና የተዘጋጁትንም የድንጋይ ቆብ ጠርቦ አመነኮሳቸውና ተሰወረ፡፡ ከእነሱም የጸኑት “እኛም አብረን ተአንተ፤” (ከአንተ አንለይም) አሉና “ሃሌ ሉያ ለአብ፤ ሃሌ ሉያ ለወልድ፤ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ!!!” ብለው እሱ ገብቶበታል ባሉት ዋሻ ገብተው ተሰውረው ቀሩ፡፡ ገዳሙም አብረንታንት መድኃኔዓለም ተባለ፡፡ አንተን ስንከተልህ፣ ስናመልክህ እንኖራለን፣ ካንተ ወዴት እንሔዳን ማለታቸው ነው፡፡ በእርግጥም ይኼው ለብዙ ክፍለ ዘመናት ሁሌም ኢየሱስ ክርስቶስ በፊታቸው እንደተሰቀለ ሁኖ የሚታያቸው፣ መከራ መስቀሉን የሚያስቡ እውነተኛ መናንያን በተጋድሎ፣ በፍቅርና በትህትና ተረዳድተው ይኖሩበታል፡፡ 
ዋልድባ በዚህ ታላቅ ገዳም ሥር ለሚጠቃለሉና በሰፊው የገዳሙ ክልል ውስጥ ለሚገኙ የዋልድባ አብረንታንት መድኃኔዓለም፣ የዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት፣ የዋልድባ ዳልሽሐ ኪዳነ ምሕረት እና ለሌሎችም በርከት ላሉ የገዳሙ ቦታዎች የሚያገለገግል የጋራ ስም ሲሆን አብረንታት መድኃኔዓለም ደግሞ ዋናው ገዳም ነው። ጌታ የተሰወረበት ዋሻ ከገዳሙ የሁለት ሰዓት ያህል መንገድ የሚወስድ ሲሆን ዛሬም ድረስ በምእመናን ይጎበኛል፡፡ አፈሩ ድውያንን ይፈውሳል፡፡ የዋሻው መጨረሻ ስለማይታወቅ አባቶች በድንጋይ ካብ የዘጉትን በጨለማው ዋሻ ውስጥ ዳስሼ ተመልክቻለሁ፡፡ 

ማዬ-ዮርዳኖስ ዘዋልድባ”

የዋልድባ ገዳም ጸበል ማየ-ዮርዳኖስ ትባላለች፡፡ ባለቤቱ መድኃኔዓለም “እንደ ተጠመቅሁባት እንደ ዮርዳኖስ ትሁንላችሁ” ብሎ ባረኳታል። ጸበሏ ለክብረ በዓሉ የሚመጣው ያ! ሁሉ ሕዝብ ሲጠመቅባት ቢሰነብትም ትንሽ እንኳ አትጎድልም። ኋላም ለእርሱና ቤት ለቀሩ ወገኖቹ ፈውስ ትሆነው ዘንድ ገጠሬው በቅልና ቅምጫና ከተሜው በጀሪካን እየሞላ ይወስዳል። ማየ ዮርዳኖስ ግን አሁንም ድረስ አንድ ኩባያ የተቀዳባት አትመስልም። መጉደል ዐታውቅም፤ ሁሌም ሙሉ። የሚቀዳት ቢጠፋም ሞልታ አትፈስም፡፡ የኔ ብጤ ደፋርና ሳያዩ ከሚያምኑት ወገን ለመሆን የሚቸገር እልከኛ ኅሊና ያለው በስተምሥራቅ በኩል ባለችው የጸበል ቤቱ ብቸኛ መስኮት ብቅ ብሎ ለአፍታ ማየት ይችላል። የሰማውን በዐይኑ ዐይቶ ለማረጋገጥ።

ታዲያ ጸበሏን ለመቅዳት አይደለም፤ ወደ ጸበል ቤቱ ለመግባት ካህን መሆን ብቻ በቂ አይደለም። መነኮስ መሆንም የፈቃድ ወረቀት ማግኘት ማለት አይደለም። ይልቁንም ሥምረት የተነሣ የማኅበረ መነኮሳቱ አባል መሆን አለበት። ሥምረት ማለት በዋልድባ ገዳም ብቻ ያለ ገዳማዊ ሥርዐት ነው። መነኮሱ ይህ ሥርዐት ሲፈጸምለት ነው የታላቁ ገዳም አባል የሚሆነው። ከማኅበረ መነኮሳቱ የሚቆጠረው፤ ደቀ-ሳሙኤል የሚባለው። ነፍሱን ይማረውና አያቴ አያይ ከዐርባ ዓመት በፊት ወደ ገዳሙ ወርዶ ነበር፡፡ በጊዜው አንድ ያልተፈቀደለት ሰው ወደ ጸበል ቤቱ በመግባቱ ምክንያት ጸበሏ መድረቋንና ከብዙ ምህላ በኋላ እንደገና መፍለቅ እንደጀመረች፣ በዚያ ቀንም በርካቶች እንደተፈወሱ በዐይኑ ያየውን መስክሮልኛል።
🌻🌻🌻🌻🌻🌻🌻🌻
#ዋልድባ_ፀጥታና_ነፍስ_የቆረቡበት_ገዳም!

አብረንታንት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ውስጥ ከሚገኘው አንድ ዛፍ ላይ የተንጠለጠለ ደወል አለ። ደወሉ የትም ቦታም እንደምናገኛቸው ዓይነት ደወሎች ከብረት የተሠራ አይደለም፤ ከጣውላ እንጂ። ይህ ደወል በየባዕታቸው በጸሎት የሚተጉትን፣ ለሥራ የተሰማሩትን መነኮሳት ለጸሎተ ማዕድ፣ ሌሊት ሌሊት ደግሞ ለሰዓታት፣ ለኪዳን የሚጠራ የቤተክርስቲያንዋ ድምፅ ነው።

በዓሉ በሚከበርበት ሳምንትም በየሰዓቱ ከሚደወለው የዚህ ደወል ድምፅና የምእመናኑ ምህላ በቀር ሌላ ጩኸት ከፍ ባለ ድምፅ ሲሰማ አባቶችን አያስደስትም። በበዓሉ የታደመው ምእመን ሁሉ የቆየውን ገዳማዊ አኗኗር ማክበር አለበት። በዙሪያው የተሰወሩ በርካታ ቅዱሳን የሞሉበት ምድር ነውና ያልተለመደ ጩኸት በጸሎት ላይ ያሉ በርካታ መናንያንን ያውካል ተብሎ ስለሚታሰብ ክልክል ነው። ስለዚህ መዝሙር መዘመር ምስጋና ነውና ችግር የለም በሚል እሳቤ ሰብሰብ ብለው ቢጀምሩ የመጀመሪያው የተግሣፅ ቃል የሚመጣብዎት አጠገብዎ ካረፉ ተሳላሚዎች ነው። ይህንን ተግሳጽ ቸል ብለው ቢቀጥሉ ከገዳማዊያኑ አንዳች ክልከላ አይመጣብዎትም። ብቻ ኀዘናቸውን ያበዙታል እንጂ።

በገዳሙ ውስጥ ቅዳሴ እንኳ የሚቀደሰው በዓመት አምስት ጊዜ ብቻ ነው። እነርሱም የመጋቢት መድኃኔዓለም፣ የሆሳዕና፣ የትንሣኤ፣ የጥምቀት እና የሐምሌ አቦ በዓላት ናቸው። ከዚህ ውጭ ኪዳን ይደርስበታል፣ሰዓታት ይቆማል፣ የመነኮሳቱ የማኅበር ጸሎት አይስታጎልም። መቼም የአክሱም ጽዮንን 365 ቀናት የማያቋርጥ የቅዳሴ አገልግሎት የሚያውቅ ሰው በዓመት አምስት ጊዜ ብቻ የሚቀደስበትን የዋልድባን ታሪክ ሲሰማ ሊገረም ይችላል። እውነቱ ግን ይህ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ገዳሙ ለተጋድሎና ለጥሞና የተሰበሰቡ መናንያን ባዕት በመሆኑ ነው።

***

አንድ ሽማግሌ የጌታን ሥዕለ አድኅኖ (አክሊለ ሶክ) እና ሥዕለ ማርያም ለአንድ አባት እንድናደርስላቸው አደራ አሉን፡፡ መልእክቱን የምናደርስላቸው አባት ባዕት ከአብረንታንት መድኃኔዓለም ሠላሳ ደቂቃ ያህል ይወስዳል(ስሙን ካልተሳሳትኩ ማይ ሎሚ መሰለኝ የሚባለው)፡፡ አርድእት እንዳንረብሻቸው አስጠንቅቀው መንገዱን አመላከቱን፡፡ ከጓደኞቼ ጋር ሔድን፡፡ የሎሚና የሰርኪን ዛፍ በሚበዛበት ጥቅጥቅ ያለ ደን ውስጥ አንዲት በዓት አገኘን፡፡ በገዳሙ ሥርዐት መሠረት በተወሰነ የጊዜ ክፍተት ውስጥ ሦስቴ አጨበጨብን፡፡ መልስ የለም፡፡

ከአንድ ሰዓት በላይ ጠበቅን፣ ብቅ ያለ ሰው የለም፡፡ በመጠበቅና ቶሎ በመመለስ መካከል እያወላወልን ሳለን አንዲት ሎሚ ከተጠጋናት ዛፍ ተቆርጣ አጠገባችን ወደቀች፡፡ ማጅላን የምንለው ጓደኛችን ተሸቀዳድሞ አነሣት፡፡ “እንዴ ሰሌ!? ይኸ እኮ ገዳም ነው፤ ያውም ዋልድባ፡፡ ወድቆ አግኝቻለሁ ብለህ ብትወስድ በርሐው ውስጥ ወድቀህ ትቀራለህ እንጂ ቤትህ አትገባትም፡፡” ወረጠበ የምንለው(ተፈሪ አበራ) ማጅላንን አስጠነቀቀው፡፡