Dn Abel Kassahun Mekuria
15.2K subscribers
531 photos
44 videos
1 file
841 links
ይህ ኦርቶዶክሳዊ የሆኑ የተለያዩ ትምህርቶችን የሚያገኙበት በባለቤቱ የተከፈተ ቻነል ነው።

ይወዳጁን

ለፌስቡክ ገጽ
https://www.facebook.com/AbelKassahunMekuria12?mibextid=ZbWKwL

ለyoutube
https://youtu.be/s6Cn-jMYjrk?si=Tw7lXr62xkGQtL9_

ለInstagram
https://www.instagram.com/abelkassahunm?igsh=OW
Download Telegram
    +++ "እየጠላን የምናደርገው" +++

ብዙ ሰው ‹‹እኔ ሐሜት አልወድም፡፡ ግን ማማት የሚወዱ ጓደኞች አሉኝ›› ይላል፡፡ አሁን እርሱ ምን እያደረገ ነው? ‹‹ወዳጆቼ ሐሜተኞች ናቸው›› ሲል እያማቸው አይደለምን? ወይስ ለእርሱ ሲሆን ሐሜቱ ተለውጦ የመረጃ ቅብብል ይሆናል?! በነገራችን ላይ ይህ የዚህ ጽሑፍ መግቢያ ራሱ ሐሜት ነው።

የማንወደው ነገር ግን እየጠላንም ቢሆን የምናደርገው ኃጢአት ሐሜት ነው፡፡  በመጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ ሐሜተኛ ሆኖ  የተጠቀሰው በእባብ ያደረው ሰይጣን ነው፡፡ በመጀመሪያ የታማው ደግሞ  እግዚአብሔር ሲሆን፣ ሐሜቱን ሰምታ ሳትመረምር የተቀበለችውና ለስሕተት የቸኮለችው ሴት  ሔዋን ነበረች፡፡(ዘፍ 3፥1-5)

   የሰይጣን ሐሜት እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ አንደኛ "አትሞቱም፤ እንደ እርሱ እንዳትሆኑ ነው የከለከላችሁ" በሚለው ንግግሩ "እግዚአብሔር ዋሽቷችኋል" እያለ ፍቅሩን እንድትጠራጠር እያደረገ ነው። ሁለተኛ ደግሞ ከዛፉ ብትበሉ እንደ እርሱ ትሆናላችሁ በማለት የእግዚአብሔር አምላክነት "የዛፍ ፍሬ" በመብላት የተገኘ መሆኑንና እርሱም እንደ እነርሱ የነበረበት ጊዜ እንዳለ እንድታስብ እየገፋፋት ነው። ታዲያ ከዚህ በላይ ስም ማጥፋት (Character assassination) ከየት ሊገኝ ይችላል? ሰይጣን በነገር ሁሉ ፍጹም የሆነን አምላክ ጆሮን ጭው የሚያደርግ ሐሰት ፈጥሮ ለማማት ወደ ኋላ ካላለ፣ አንዳች ጉድለት የማያጣብን እኛማ ከሐሜቱ ጅራፍ ልናመልጥ እንደማንችል ሊታወቅ ይገባል፡፡

በተለይ በአሁን ጊዜ ሐሜት በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ሥሩን ሰድዷል። እንደውም ባልንጀራን ማማት እንደ ምግብ ቢሆን ኖሮ ብዙዎቻችን በዚህች ደሃ አገር ከመጠን በላይ ወፍረን እንቸገር ነበር። ማኅበራዊ ሚዲያዎቻችን የሐሜት አውድማዎች ሆነዋል። በየገጾቻችን ከሽነን የምናቀርባቸው ጽሑፎች ጠረናቸው የሰው ሥጋ የሰው ሥጋ ይላሉ። ፊታችን በሐሜት ወይቦ ሁለት መልክ ካወጣን ቆየን። ይኸው ሳንባችን በማማት አየር ተመርዞ ሳሉ ከበረታብን ሰነባብተናል። ወዳጃችንን የማናማበት ብቸኛው ጊዜ ከእርሱ ጋር የምንሆንበት ሰዓት ነው። ያውም ደግሞ ያንኑ ጊዜ ሌላኛውን ሰው ለማማት ካልተጠቀምንበት ማለቴ ነው።

ሊቁ ዮሐንስ ካዝያን እንደሚናገረው ሰው ከሚጠቅመው ቃለ እግዚአብሔር ይልቅ የማይጠቅመው ሐሜት ያጓጓዋል። የአምላክ ቃል ሲነገር እንቅልፍ እንቅልፍ የሚለው ሁሉ፣ የሐሜት ነገር ሲሆን ግን እንደ እርሱ ንቁ የሚሆን የለም። በጥፍሩ ቆሞ ይሰማል። ሌሊቱን ሁሉ ሳይተኛ ቢያድር ደስ ይለዋል።

ለመሆኑ ባልንጀራችንን ስለ ምን በቀስታ እናማዋለን? የወዳጃችንንስ ውድቀት በማውራት በእኛ ላይ የምንጨምረው ምን በጎ ነገር አለ? በሰው ፊት መልካም እየመሰልን ከኋላው ግን ስለ እርሱ ውድቀት በማውራት የራሳችንን ደረጃ ከፍ ማድረግ አይቻልም። ስለ ሌሎች በማውራት የምናጠፋውን ሰዓት ራሳችንን ለማሳደግ ብንጠቀምበት ኖሮ "መኖራችንን ትርጉም እንዲኖረው" ማድረግ ይቻለን ነበር።

"ንጹሕ ወዳጅነት" ሐሜትና ማሾክሾክ የሌለባት የታማኞች ጌጥ ናት። የሐሜት ስለታቸውን ያልጣሉ ሰዎች "እውነተኛ ባልንጀርነት"ን አያውቋትም። አንተ በፍቅር ወዳጅ አድርገህ ከፊትህ ስታቀርባቸው እነርሱ ከኋላህ ሆነው የሚያሙህን አትጥላቸው፤ አትጣላቸው። ነገር ግን የሐሜቱ እርሾ እንዳያገኝህ ቶሎ ተለያቸው። ከፊትህም አድርገህ አታሰቃያቸው። የእነርሱ ቦታ ከኋላህ መሆን ነው።

ሐሜት የሰይጣን ነው። ሰውን የሚያማ በገዛ ፈቃዱ አንደበቱን ለሰይጣን አሳልፎ የሰጠ ነው። ማማት በቤተ ክርስቲያን መለያየትን ያመጣል፣ ቤተሰብ ይበትናል፣ ወንድሞችን ያጣላል። ብንችል ስለ ሰው የምናውቀውን ጥሩውን እናውራ። የምናወራው ጥሩነት ከሌለው ደግሞ ቢያንስ ምንም አንበል።

ሔዋን ልክ እንደ አዳም እባብን "ሂጅልኝ" ብላ ብታባራት ኖሮ እነርሱም ከፈጣሪ ባልተጣሉ ሐሜትም ወደ ዓለም ባልገባ ነበር። ሐሜትን ማጥፋት ከፈለግን ሐሜተኛን እሺ አንበል። ማር ይስሐቅም "ወዳጁን በፊትህ የሚያንኳስሰውን ሰው አፉን መዝጋት ባትችል እንኳን ቢያንስ ሐሜቱን ከመስማት ተቆጠብ" ይላል። ሐሜትን ደስ ብሎህ ካልሰማኸው ደስ ብሎት የሚያማን ሰው ልትፈጥር አትችልም።


"ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱ ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ" ገላ 5፥15



ዲያቆን አቤል ካሳሁን

https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
Dn Abel Kassahun Mekuria pinned «#ትሕትና ምን ማለት ነው? #ሰው ትሑት የሚባለው መቼ ነው? #ትሕትና በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ የሚኖረው ቦታ ምን ያህል ነው? መልሶቹ በዚህ አጭር ደቂቃ ትምህርት ውስጥ ይገኛሉ። https://youtu.be/_pCuZ0LQSW4»
የልደት ቀኔን በማስመልከት መልካም ምኞቶቻችሁን ላፈሰሳችሁልኝ ሁሉ፣ መድኃኔዓለም የእናንተንም ዕድሜና ሕይወት ለእኔ እንደ ተመኛችሁት እንዲሁ ያድርግላችሁ። መወለድ ጥሩ ነው፣ የተወለዱበትን ዓላማ አሳክቶ ወደ ፈጣሪ መሄድ ደግሞ እጅግ የሚሻል ነው። የውልደት ማረጋገጫ ልደቴን ይኸው በዓመት በዓመት እያከበርኩ ነው። ለዘላለም ሕይወት በክብር የምወለድበትን መልካሙን ሥራ እንድሠራ እና ፍጻሜዬ ድል ከነሡ ቅዱሳን ጋር እንዲሆንልኝ በ"ጸሎተ ማርያም" አትርሱኝ።
በማርቆስ ወንጌል ላይ ተጽፎ እንደ ምናነበው ጌታ ያደረጋቸውን ታላላቅ ተአምራት እየሰሙ ብዙዎች ከተለያዩ ቦታዎች እርሱ ወዳለበት ይመጡ ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስም የተሰበሰቡት ሰዎቹ እንዳያጋፉት ታንኳ ያዘጋጁለት ዘንድ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው፡፡(ማር 3፥7) የሚገርመው ከዚህ ታሪክ መፈጸም በፊትም ሆነ በኋላ ጌታችን በብዙ ሰዎች መካከል ተከቦ አስተምሯል፡፡ የልብሱንም ጫፍ ለመዳሰስ የለመኑትን ሳያሳፍራቸው ዳሰሰዉት እንዲፈወሱ አድርጓል፡፡ አሁን ግን ሰዎቹ ‹እንዳያጋፉት› ሐዋርያቱ ታንኳ እንዲያዘጋጁለት አዘዘ፡፡ ልብ በሉ ‹እንዳይዳስሱት› አላለም፣ ‹እንዳያጋፉት› እንጂ፡፡ ይህ ስለ ምን ሆነ? ካላችሁ፣ ልብሱን ለመዳሰስ የሚቀርቡት ሰዎች አቀራረባቸው ‹በልመና›/‹በጸሎት› ሲሆኑ፣ የሚጋፉት ሰዎች ግን ቃሉም እንደሚገልጸው ወደ እርሱ ለመቅረብ የሚሞክሩት በጉልበታቸው ነው፡፡ ስለዚህ በትሕትና ሆነው ለሚለምኑት ቅርብ ሆኖ ሲዳሰስላቸው፣ በጉልበታቸው ለሚጋፉት ግን ሊደርሱበት ወደማይችሉት ባሕር ተሳፍሮ ይርቅባቸዋል፡፡ እግዚአብሔርን በእምነት ብርሃንነት ስትፈልገው ቅርብ ሆኖ ታገኘዋለህ፡፡ በራስህ ማስተዋል ግን በመደገፍ ላስሰው ብትል መሰወሪያውን ጨለማ ያደርግብሃል፡፡

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
https://tttttt.me/Dnabel
https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
ለንስሐ ጥሪ ቀጠሮ አንስጥ። መጠየቅን ወደሚወድ አምላክ የምንሄድበትን ጊዜ አናውቅምና ዘወትር ለመልካም ነገር የተነሣሣ ልቡና ይኑረን። "ንስሐ ግቡ፣ ቁረቡ" ስንባል "ወጣት አይደለሁ? ገና ምኑን አየኹትና? ቆይ ትንሽ!" እያልን መንፈሳዊነትን ከኃጢአት በተረፈ ጉልበት የሚሠራ የጡረታ ሥራ አናድርገው። የተመረጠውን የወጣትነት ዕድሜ ለበደል ሳይሆን ለጽድቅ እናውለው።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
+++የሕፃናት ጥምቀት+++

አዳምና ሔዋን ሕግ አፍርሰው ከተከለከሉት ዛፍ ፍሬ ከበሉባት ሰዓት ጀምሮ ጸጋ እግዚአብሔርን ተገፈው እርቃናቸውን ቀርተዋል፡፡ በወቅቱም የተሰማቸውን እንግዳ የሐፍረት ስሜት መቆጣጠር ስለተሳናቸው ዕርቃናቸውን የሚሸፍኑበትን ቅጠል በገነት ካሉት ዛፎች ቆርጠው በሰውነታቸው ላይ አገለደሙ፡፡ እግዚአብሔርም ከገነት ባስወጣቸው ጊዜ ያገለደሙት የቅጠል ስፌት የዚህን ዓለም ብርድ እንደማይቋቋምላቸው ስላወቀ ከእንስሳት ለምድ የተዘጋጀ የሚሞቅ የቁርበትን ልብስ አለበሳቸው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም የሰው ልጅ ሁሉ ልብስ ያስፈልገው ጀመር፡፡ የዕድሜ ክልል ገደብ ሳይኖረው አረጋዊውም ፣ዛሬ የተወለደውም ሕጻን በጨርቅ የሚጠቀለል ሆነ፡፡

ማንኛውም ሕፃናት ልጆች ያሉት ጤናማ ወላጅ ልጆቹ የልብስን ጠቀሜታ ስላልተረዱ ‹አድገው እስኪረዱት ድረስ እርቃናቸውን ይቆዩ› በማለት እንደማይተዋቸው የታወቀ ነው፡፡ ምንም ክፉና ደጉን ባይለዩ፣ ራቁት የመሆን የሐፍረት ስሜት ባያሸንፋቸውም ፤ ከጤናቸው አንጻር በብርድ እንዳይታመሙበት ሲል ለልጆቹ በማሰብ ልብስ ያለብሷቸዋል፡፡

የሰው ልጅ ሥጋዊ ወይም ቁሳዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊም ፍጥረት ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ለግዙፍ ሥጋው መጎናጸፊያ ልብስ እንደሚያስፈልገው ፤ ለረቂቅ ነፍሱም ልብስ ያስፈልጋታል፡፡ በልብስ ያልተሸፈነ ሰውነት ለብርድና ለተለያዩ በሽታ አምጪ ሕዋሳት እንደሚጋለጥ ፣እንዲሁ በልብስ ያልተሸፈነች ነፍስም በኃጢአት ከሚመርዟት አጋንንት ማምለጥ አትችልም፡፡ ታዲያ ይህ የነፍሳችን ልብስ ምንድር ነው? እንዴትስ ነው የምትለብሰው?

ድንኳን ሰፊ የነበረው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ነፍሳችን ስለምትለብሰው ረቂቅ በፍታና ስለምትለብስበትም መንገድ ምንነት ለገላትያ ሰዎች በላከው መልእክቱ ‹የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋል› ሲል ይናገራል (ገላ 3፡27)፡፡ ከዚህም የሐዋርያው ትምህርት በመነሣት የነፍስ ልብስ የተባለው ‹ክርስቶስ› ሲሆን ፤ እርሱን የምንለብስበት መንገድ ደግሞ ‹ጥምቀት› መሆኑን እንረዳለን፡፡

በዛሬ ጽሑፋችን ምሥጢራትን በመመገብ የእናትነት ድርሻዋን የምትወጣው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ለምን በሕፃንነት ዕድሜያችን እንድንጠመቅ እንደምታደርገን በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡ ብዙ ጊዜ ይህ ርዕሰ ጉዳይ ሲነሣ በተቃራኒ የትምህርት ጎራ ውስጥ ያሉ ወንድሞቻችን ከሚያቀርቧቸው የተቃውሞ አሳቦች መካከል ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡ አንደኛው ‹ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ› የሚለውን የቅዱስ ጴጥሮስን የስብከት ቃል ይዘው ‹እነዚህ የምታጠምቋቸው ሕጻናት ምን ኃጢአት አለባቸው?› ሲሉ የሚጠይቁት ሲሆን ፣ሁለተኛው ደግሞ ‹ገና ሕጻናት ሲሆኑ ምን አውቀው ነው ያለ ፈቃዳቸው የምታጠምቋቸው?› የሚል ከማወቅ ጋር የተያያዘ ጥያቄ ነው፡፡(ሐዋ 2፡38)

የመጀመሪያው ጥያቄ የጥምቀትን ጥቅሞች ካለመረዳት የመጣ ጥያቄ ይመስላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ጥምቀት ከሚፈጸምባቸው ምክንያቶች አንዱ ለኃጢአት ስርየት እንደሆነ ቢናገርም ‹ለኃጢአት ሥርየት ብቻ› ግን አይልም፡፡ ከሁሉም በላይ በጥምቀት የምናገኘው ትልቁ ጸጋ ‹ልጅነት›ን ነው፡፡ ስለዚህም ታላቅ ጸጋ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአይሁድ አለቃ ለኒቆዲሞስ ‹ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ… › በማለት በጥምቀት ስለሚገኘው የእግዚአብሔር ልጅነት አስተምሮታል፡፡(ዮሐ 3፡5) ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እንደሚናገረው ቤተ ክርስቲያን ሕጻናትን የምታጠምቀው ኃጢአት ፣በደል አለባቸው ብላ ሳይሆን ፤ ከለጋነት ዕድሜያቸው ጀምረው ፍቅሩን እያጣጣሙ እንዲያድጉ የሚያስችላቸውን የእግዚአብሔር ልጅ የመሆንን ጸጋ ልትሰጣቸው ነው፡፡

ወደ ሁለተኛው ጥያቄ ስንመጣ በራሱ በጥያቄው መነሻ አሳብ ላይ የምንመለከተው እንደ ገደል የሰፋ ክፍተት አለ፡፡ ይህም ክፍተት ጥያቄውን የሚጠይቁ ሰዎች የተነሡበት ‹ሕፃናት አያውቁም› የሚለው ጭፍን መንደርደሪያ ነው፡፡ እነርሱ ‹ሕጻናት እንደማያውቁ በምን አወቁ? አንድ ሕፃን ስላልተናገረና አሳቡን በቃላት ስላልገለጸ ብቻ አያውቅም ሊባል ይችላል? ፡፡ እንዲህ ካሉ ደግሞ የጌታ እናት እመቤታችን ወደ እርሱ እንደቀረበች አውቆ በስግደት የደስታውን ስሜት ስለገለጸው የስድስት ወር ፅንስ ምን ይላሉ? ሳያውቅ ነው የዘለለው ሊሉን ይሆን? ቢቀበሉ ደግሞ ይህን የመሳሰሉ ድንቅ ማስረጃዎችን ከቅዱሳን አበው ገድላት እናቀርብላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን እንኳን የአዋልዱን ይቅርና የአሥራው መጻሕፍቱንም ምስክር ለማመን ስለሚቸገሩ ማስረጃ አናባክንም፡፡

ታዲያ እነዚህን ጥያቄዎች ስንጠይቅ እኛ ደግሞ በተቃራኒው ሕጻናት ያውቃሉ ወደሚል ሌላ ጽንፍ እያመራን አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሕፃናትን የምታጠምቀው ያውቃሉ ወይም አያውቁም ብላ አይደለም፡፡ የቤተሰቦቻቸውን እምነት ምስክር በማድረግ ነው እንጂ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በልጅነታቸው ጥምቀተ ክርስትና የተፈጸመላቸው እንዳሉ የሚያሳዩ ልዩ ልዩ የንባብ ክፍሎች አሉ፡፡ ለአብነትም በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በተመሳሳይ ምዕራፍ ላይ የምናገኛቸውን ሐር ሸጯ ልድያንና የወኅኒ ቤተ ጠባቂውን ማቅረብ እንችላለን፡፡ መጽሐፉ ሁለቱም ሰዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንደተጠመቁ ይናገራል (ሐዋ 16፡15 ፣34)፡፡ ታዲያ ከቤተሰቦቻቸው መካከል ሕፃናት ሊኖሩ አይችሉምን?

ሌላው በበዓለ ሃምሳ ከተሰጠው የቅዱስ ጴጥሮስ ስብከት ውስጥም ስለ ሕፃናት ጥምቀት የሚናገር ግልጽ ማብራሪያ እናገኛለን፡፡ ይኸውም ‹ኃጢአታችሁ ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ… የተስፋው ቃል (ተጠምቆ መንፈስ ቅዱስን መቀበል) ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ነውና› የሚለው ሲሆን በዚህ አረፍተ ነገር ውስጥ ‹ለልጆቻችሁ› የሚለው ቃል ያለ ማብራሪያ ጥምቀት ለሕፃናት እንደሚፈጸም የሚያሳይ ነው፡፡(ሐዋ 2፡38-39) ጌታችንም በወንጌል ‹ሕፃናትን ተዉአቸው ፤ ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሉአቸው› ሲል የተናገረውን ቃል እንዴት እንረዳዋለን? ሕፃናት ወደ እግዚአብሔር እንዴት ይቀርባሉ? ሕፃናት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ የሚችሉት በምሥጢራት (Sacraments) ነው፡፡ ታዲያ ከምሥጢረ ጥምቀት የበለጠ ሕፃናት እና አምላክን በአባትና ልጅነት የሚያቀራርብ ምን አለ? ሕጻናት እንዳይጠመቁ ከመከልከል የበለጠስ እነርሱን ከፈጣሪ የማራቅ ሥራ ከየት ሊገኝ ይችላል?፡፡(ማቴ 19፡14)

እነ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮትም ቅዱስ ጳውሎስ ለጥምቀት ምሳሌ አድርጎ ያነሣውን የግዝረት ሥርዓት ለሕፃናት ጥምቀት ማስረጃ አድርገው አስተምረውበታል፡፡ በአብርሃም ዘመን ግዝረት የእግዚአብሔር ሕዝብ ወይም ወገን ለመሆን ምልክት ነበር፡፡ ስለዚህም በአብርሃም ቤት የሚወለዱ ሕፃናት ስምንት ቀን ሲሆናቸው እንዲገረዙ ሕግ ወጥቷል፡፡(ዘፍ 17፡10-14) ሕፃኑም በዚያ የቀናት ዕድሜ ላይ እያለ ይገረዛል እንጂ ቆይ ይደግና ጠይቀነው አይባልም፡፡ ልክ እንደ ግዝረቱ በሐዲስ ኪዳንም ጥምቀት ከእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ጋር በሕዋስነት የምንቆጠርበት ምሥጢር ነው፡፡ ግዝረት በሕፃንነት ይፈጸም እንደነበር፣ ጥምቀትም በሕፃንነት ይፈጸማል፡፡ እንደ ቅዱስ ጎርጎርዮስም አባባል ‹የጣቶቻቸው ጥፍር ሳይጸና› በጨቅላነት ዕድሜያቸው ይጠመቃሉ፡፡ ይኸው ሊቅ ሌላው የጥምቀት ምሳሌ የሆነውን
ባሕር መሻገር በማንሣት ፣ ባሕሩን የተሻገሩት ሕፃናትም ጭምር እንደሆኑ ፣ጥምቀተ ክርስትናም ለሕፃናት ይፈጸማል ሲል ይናገራል (1ኛ ቆሮ 10፡1-2)፡፡

ጥምቀተ ክርስትና ሁል ጊዜ ተጠማቂው ተጠይቆ ላይፈጸም ይችላል፡፡ ለምሳሌ የመጀመሪያው ሰው አዳም የተፈጠረው የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አዳምን ከፈጠረው በኋላ በአፍንጫው የሕይወት እስትንፋስን እፍ ብሎበታል፡፡ ይህም እፍታ ለአዳም የልጅነትን ጸጋ ያገኘበት ጥምቀቱ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን ታሪክ በያዘው የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ እግዚአብሔር ለአዳም የልጅነት ጸጋውን ከመስጠቱ በፊት እንደ ጠየቀው አይናገርም፡፡ ታዲያ እንዴት የሠላሳ ዓመቱ ጎልማሳ አዳም ያልተጠየቀውን ጥያቄ የአርባን ቀን ልጅ ጠይቁ ይሉናል? ፡፡ እግዚአብሔር አዳምን አልጠየቀውም ማለት አስገደደው ማለት አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ሕፃናትን በቀጥታ እነርሱን አልጠየቀችም ማለት አስገድዳቸዋለች ማለት አይደለም፡፡ አዳም የኋላ ኋላ በፈቃዱ ፈጣሪውን ክዶ ልጅነቱን እንዳጣ እንዲሁ የእግዚአብሔርን አባትነት ያልፈለጉትም አድገውም ቢሆን የመካድ መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡

ሌላው አንዳንድ ጊዜ ከማመን (ከትምህርት) ጥምቀት ሊቀድም የሚችልባቸውም ሁኔታዎች እንዳሉ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያቱን ወደ ዓለም ሲልካቸው ‹ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው› ሲል ያዘዛቸው (ማቴ 28፡19)፡፡ ልብ በሉ በዚህ የጌታችን ትዕዛዝ ውስጥ በቀዳሚነት የተነገረው ‹አስተምሩ› የሚለው ሳይሆን አጥምቁ የሚለው ነው፡፡ ስለዚህ አድገው ወደ ቤተ ክርስቲያን ለሚገቡ ካልሆነ በቀር ለሕፃናት ጥምቀት ሊቀድም ይችላል፡፡ ደቀ መዝሙርነት የሚገኘው ከጥምቀት በኋላ ነው፡፡ ሳይጠመቁ ደቀ መዝሙርነት የለም፡፡

በአጠቃላይ ከላይ ያቀረብናቸው ነጥቦች የሕፃናትን ጥምቀት ተገቢነት የሚያሳዩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶች ሲሆኑ በተቃራኒው ግን የሕፃናትን ጥምቀት የሚከለክል ምንም ዓይነት ትምህርት ወይም ማስረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ አናገኝም። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያናችን በዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተግባሯ ብትመሰገን እንጂ የምትነቀፍ አይደለችም።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን

https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
ስምሽን ስጠራ ልቡናውን እንዳያጸናብኝ ዐውቄ አምኜ ወደ ልጅሽ እጄን እዘረጋለሁ፡፡ ስምሽን በመጥራት ስለምነው ምሕረቱ አይዘገይብኝም፤ ይቅርታውንም ዐውቀዋለሁ፡፡

እኔ ገደሉን ለማለፍ ወደ ብርሃን ሥፍራ ለመድረስ የቸኮልሁ ነኝ፡፡ አንቺ የመድኃኒት ድልድይ ነሽ፡፡ ልጅሽም ለተገፉት መጠጊያ የተድላ ደስታ ሥፍራ ነው፡፡

የመለኮትን ዕንቁ ለመግዛት እኔ ነጋዴ ነኝ፡፡ አንቺ የሕይወት መርከብ ነሽ፡፡ ልጅሽም የበጎ ነገር ሁሉ ድልብ በውስጡ ያለበት የትርፍ ሥፍራ ነው፡፡

እኔ የመንፈስ ቅዱስን ሀብት የምፈልግ ደሃ ነኝ፡፡ አንቺ የክብር ሁሉ መከማቻ ነሽ፡፡ ልጅሽም ለባለሟልነትና ለክብር ለማሞገስ የሽልማት ጌጽ ነው፡፡

እኔ የታረዝሁ የብርሃን ልብስ የምሻ ነኝ፡፡ አንቺ የሸማኔ ዕቃ ነሽ፡፡ ልጅሽም የማያልቅ የማያረጅ የሃይማኖት ልብስ ነው፡፡

እኔ ቁስለኛ ነኝ አንቺ የመድኃኒት ሙዳይ ነሽ፡፡ ልጅሽም ባለ መድኃኒት ነው፡፡

===========

የፍቅሯ ኃይል ያረፈበት የስም አጠራሯ ከአንደበቱ የማይለየው አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ

በጸሎቷ የምናምን ሁላችንንም በቃል ኪዳኗ ጥላ ትከልለን!!!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
Dn Abel Kassahun Mekuria pinned «https://youtu.be/4AVBAhcMCic»
በዓይን ቀልድ የለም። አንዳች ወደ አንተ የሚወረወር ባዕድ ነገር ብታይ ቀድመህ በእጆችህ የምትከላከለው ዓይንህ ያለበትን አካባቢ ነው። ለምትወደው ሰው እንኳን ያለህን ደጀንነት ስትገልጽ "በአንተ/ቺ የመጣ በዓይኔ መጣ" ትላለህ። መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊትም አምላኩን "እንደ ዓይን ብሌን ጠብቀኝ" እያለ ይማጸናል።(መዝ 17፥8) ዓይን ነዋ!

በሰውነታችን ካሉት ሕዋሳት ውስጥ ከናላ (brain) ቀጥሎ በጣም ውስብስብ የሆነው ሕዋስ ዓይን ነው። ትንሽ መጠን ባላት ዓይን ውስጥ የፈሰሰውን የፈጣሪ ጥበብ ስትመለከት እጅህን በአፍህ ትጭናለህ። በነገራችን ላይ እግዚአብሔር የለሹ ዳርዊን እንኳን ዓይን "በተፈጥሮ ምርጫ"/Natural selection/ ነው የተገኘው ብሎ ለማመን እንደሚቸገርና ሁኔታው ወለፈንድ(absurd) እንደሚሆንበት ተናግሯል። ምን ያድርግ!

ዓይን በሌሎች እንስሳትም ዘንድ ያለው ቦታ የሚናቅ አይደለም። ሰጎን በመጠን ከናላዋ የሚበልጥ ዓይን አላት። ይገርማል :-)

በተለያዩ ፍጥረታት ዘንድ የሚገኙ ዓይኖች የእነዚያን ፍጥረታት ፍላጎታቸውን እንዲያሟሉ ተደርገው የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የሰው ልጅ አንድን ምስል አጥርቶ እና በዝርዝር ማየት ይፈልጋል፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር የሰውን ዓይን በከፍተኛ ጥራት እንዲያይ አድርጎ ነው ያዘጋጀው፡፡ እንደ ሳይንሱም ጥናት ከሆነ የሰው ልጅ አጥርቶ የማየት ችሎታው ሜጋ ፒክስል (Mega pixel) በተባለው የመለኪያ መጠን ሲቀመጥ 576Mp ገደማ ይሆናል፡፡ ከሌሎች ፍጥረታት ደግሞ ለምሳሌ ዝንብን እንደማሳያ አድርገን እንውሰድ፡፡ ዝንብ ብዙ ጊዜ በአየር ላይ ስለምትበርር ነገሮችን በፍጥነት ማየት ያስፈልጋታል፡፡ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር ለዝንብ እንደ ሰው አጥርቶ የሚያይ ሳይሆን ፍጥነትን መቆጣጠር የሚችሉ ዓይኖችን ነው የሰጣት፡፡ ዶ/ር ካርል የተባለ አንድ ምሁር ይህንንም የዝንብ በፍጥነት የማየት ችሎታዋን ከሰው ጋር በንጽጽር ሲያስቀምጠው እንዲህ ይላል :- የሰው ልጅ በቴሌቪዥን መስኮት የሚመለከታቸው ፊልሞች ለእርሱ ከጥራት ጋር ያልተቆራረጠ ወጥ እንቅስቃሴን የሚያሳይ ትእይት ሆኖ ሲታየው፣ ለዝንቦች ደግሞ ከዓይናቸው ከፍተኛ ፍጥነትን የማየት ችሎታ የተነሣ እያዘገመ በመንሸራተት እንደሚታይ (slide show) ፎቶ ይሆንባቸዋል፡፡   Dr. Carl Wieland, M.B., B.S., in the magazine Creation ex nihilo (Vol. 18, No. 2, 1996, p. 40)


+++"እጅህ ለወሰችኝ ሠራችኝም" ኢዮ 10፥8+++


ዲያቆን አቤል ካሳሁን

https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
ሕፃናት መጠየቅ ይወዳሉ። አንዴ መጠየቅ ከጀመሩ በኋላ ደግሞ ከእነርሱ የሚወጣው "ለምን ሆነ?" የሚለው የጥያቄ ዝናብ እንዲህ በቀላሉ ቶሎ የሚያባራ አይደለም። እኛም በእነዚህ ጥያቄዎቻቸው ቶሎ ተሰላችተን ወይም ተበሳጭተን ይሆናል። ይሁን እንጂ ጉዳዩ ግን የሕፃናቱ አዲስ አእምሮ ራሱን የሚያሳድግበትና የነገ ማንነታቸውን የሚቀርጽበት ወሳኝ ሂደት ነው። የነገ ወጣቶችን ማንነት የሚቀርጹት ዛሬ "ለምን?" እያሉ ለሚጠይቁ ሕፃናት የምንመልሳቸው መልሶች ናቸው። ስለዚህ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል።

በጠና የታመመ ሕፃን ልጅ ያላት አንዲት እናት ነበረች። ይህች እናት በምትችለው ሁሉ ልጇን አሳክማና ተንከባክባ ለማዳን ብትጥርም፣ ይህ ልፋቷ ግን ሊሳካላት አልቻለም። ልጇን የያዘው በሽታ መድኃኒት ስላልነበረው ወደ ሞት አፋፍ አቅርቦታል። ታዲያ አንድ ቀን ሕፃኑ ልጅ እናቱን እንዲህ ሲል ጠየቃት :- "እናቴ፣ መሞት ምን ይመስላል? ስንሞት ያመናል እንዴ?"

በእናትየው ዓይኖች እንባዎች ሞሉ። ፊቷም በኃዘን ደፈረሰ። የረሳችው ነገር ያለ ይመስል "ቆይ መጣኹ" ብላ ሮጣ ከክፍሉ ወጣች። ብቻዋን ስቅስቅ ብላ አለቀሰች። ልጇ የጠየቃትን ጥያቄ መመለስ እንዳለባት ብታውቅም ለዚህ ለጋ አእምሮ እንዴት አድርጋ መልስ እንደምትሰጥ ግራ ገብቷታል። እንደ ምንም ራሷን አረጋግታና ጥበቡን እንዲሰጣት ወደ ፈጣሪዋ ተማጽና ተመልሳ ወደ ልጇ ክፍል ገባች።

ሕፃኑ መልሱን በጉጉት ይጠብቃል። እናትየውም የውስጧን ኃዘን ለመሰወር ለይምሰል ፈገግ ብላ እንዲህ አለችው "ልጄ፣ ታስታውሳለህ አንድ ጊዜ ጎረቤት ያለ ጓደኛህ ቤት ሄደህ ስትጫወት አምሽተህ ስለደከመህ በዚያው እንቅልፍ ወስዶህ ነበር። ከዚያም በማግስቱ ግን ስትነቃ ራስህ ያገኘኸው በመኖሪያ ቤታችን ውስጥ ስለሆነ 'እንዴት እዚህ መጣኹ?' እያልክ ስትጠይቀኝ ነበር። እኔም አባት ወደዚያ መጥቶ በጥንካራ ክንዶቹ ተሸክሞህ የአንተ ወደ ሆነው ቤትህ እንዳመጣህ ነግሬሃለኹ። አስታወስክ?"

ልጅየው :- "አዎን እናቴ"

እናትየው ቀጠለች :- "የኔ ልጅ፣ ሞትም እንደዚሁ ነው። እኛ መኖሪያችን ባልሆነች በዚህ ዓለም ሆነን እናንቀላፋለን። የሰማይ አባታችን እግዚአብሔር ደግሞ ብርቱ በሆኑ እጆቹ አቅፎ ወደ ሰማይ ይወስደናል። ከዚያም ነግቶ እንደ ገና ስንነቃ ራሳችንን በገዛ አባታችን ቤት ውስጥ እናገኘዋለን" አለችው።

እውነት ነው! ሞት ለክርስቲያኖች ሁሉ የሚኖረው ትርጉም ይህ ነው። ከእግዚአብሔር ተልከን ወደዚህ ዓለም እንደ መጣን ወደ እርሱ መመለሳችን ደግሞ የማይቀር ነው። ሞት ማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "ድንኳን" ብሎ ከገለጸው ከጊዜያዊው መቆያችን ወደ እውነተኛው መኖሪያ አገራችን መሸጋገር ነው።

በ2ኛው ክፍለ ዘመን የነበረው ግሪካዊው ፈላስፋ አርስጣደስ በጊዜው አዲስ ሃይማኖት ስለሆነበት ስለ ክርስትና እና ይህ የክርስትና እምነት በሞት ላይ ስላለው እሳቤ ለአንድ ወዳጁ በጻፈለት ደብዳቤ ላይ እንዲህ የሚል ንግግር አስፍሮ ነበር። "ከክርስቲያኖቹ ውስጥ አንድ ጻድቅ የሆነ ሰው ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይ ምእመናኑ ደስ ይሰኛሉ። ለፈጣሪያቸውም ምስጋናን ያቀርባሉ። ያም ሰው ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ቅርብ ሥፍራ የተሸጋገረ ይመስል ሰውነቱን በመዝሙራትና በምስጋና አጅበው ይሸኙታል" ይላል። ክርስትና እንዲህ ነዋ!

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ክርስቲያኖች በሞት ላይ ሊኖራቸው ስለሚገባ እይታ ሲናገር "ከእኛ መካከል አንድ ሰው በሞተ ጊዜ፣ የማያምነው ሬሳ ሲያይ ክርስቲያኑ ግን ያንቀላፋ ሰውነት ይመለከታል። ያላመነው "የሞተው ሰው ሄደ" ይላል። በርግጥ በዚህ እኛም እንስማማለን። ነገር ግን ወደ የት እንደሚሄድም እናውቃለን። የሚሄደው ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ጴጥሮስ እንዲሁም ሌሎች የቅዱሳን ማኅበር ወደ አሉበት ነው። በኋላም ተስፋ መቁረጥ ባለበት እንባ ሳይሆን፣ በክብርና በማንጸባረቅ እንደሚነሣ እናስባለን!"

+++ "ለባሪያዎችህ ሞት የለባቸውም ፍልሰት እንጂ" +++

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
https://tttttt.me/Dnabel
https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
+++ ሲዖል ምን ትመስላለች? +++

አንድ ተማሪ ወጣት እድሜ ጠገብ ወደሆኑ አረጋዊ ቀርቦ "አባቴ ሆይ ሲዖል ምን ትመስላለች?" ሲል ጠየቃቸው፣

አረጋዊውም ሲመልሱ :- ልጄ ስለዚህ ነገር የሰማሁትን አንድ ታሪክ ላጫውትህ :-

በአንድ ወቅት እግዚአብሔርን ገነት እና ሲዖል ምን እንደሚመስሉ ያሳየው ዘንድ አጥብቆ የሚለምነው አንድ የዋህ ሰው ነበር፡፡ ከእለታት በአንደኛውም ምሽት ይህ ሰው ‹ሲዖል ምን እንደምትመስል ና ላሳይህ› የሚል ድምፅን ይሰማል፡፡ ወዲያውም ምግብ የተሞላበት ማሰሮ በጠረጴዛው ላይ ካለበት እና ብዙ ሰዎች በገበታው ዙሪያ ተሰብስበው ከተቀመጡበት ክፍል ውስጥ ራሱን አገኘ፡፡ እያንዳንዳቸውም ሰዎች ዘንጋቸው የረዛዘሙ ማንኪያዎች ይዘዋል፡፡ ነገር ግን ምግቡን ምንም ከማሰሮው ውስጥ ማውጣት ቢችሉም ምግቡን የተሸከመውን የማንኪያውን ጫፍ ግን ወደ አፋቸው ማድረስ አልተቻላቸውም፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንዶቹ ያጉረመርሙ፣ አንዳንዶቹም ይጮሁ፣ ሌሎቹ ደግሞ ያለቅሱ ነበር፡፡

በመቀጠልም ያ የዋህ ሰው ‹ገነትም ምን እንደምትመስል አሳይህ ዘንድ አሁኑኑ ና› የሚል ተመሳሳይ ድምፅን ሰማ፡፡
አሁንም እንደ ቀድሞው ብዙ ሰዎች በጠረጴዛ ላይ ባለ ማዕድ ዙሪያ ከተሰበሰቡበት ሌላ ክፍል ራሱን በድንገት አገኘ፡፡ እነዚያም ሰዎች እንዲሁ ከቀድሞው ጋር ተመሳሳይ ርዝመት ያላቸውን ማንኪያዎች በእጃቸው ይዘዋል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሰዎች ጠግበው እና ደስተኛ ሆነው ይታዩ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አንዱ ሰው ማንኪያውን ወደ ማሰሮው በማጥለቅ ለእርሱ የቀረበውን ሰው በመመገብ እርስ በእርስ ይመጋገቡ ስለ ነበር ነው፡፡ 

-በዚህ ዓለም እያለህ እንዴት ራስህን በገነት የምትኖር ያህል እንዲሰማህ  ማድረግ እንደምትችል አሁን ተረዳህን? መልካምን የሚያደርግ ማንም ቢኖር ደስታ ይኖረዋል፡፡ ምክንያቱም አምላካዊ መጽናኛን ይሸለማልና፡፡ መልካም ያልሆነውን የሚያደርግ ደግሞ ስቃይ ያገኘዋል። እንደ ገነት የነበረውንም ምድር ወደ ሲዖል ይቀይረዋል፡፡

ፍቅር፣ መልካምነት በውስጥህ አሉን? እንዲህ ከሆነ አንተ ምድራዊ መልአክ ነህ፡፡ በምትሄድባቸውና በምትቆምባቸው ቦታዎች ሁሉ ከአንተ ጋር ገነትን ተሸክመሃታል፡፡

ጥልቅ የሆነ የንዴትና የብስጭትስ ስሜት ይሰማሃልን? ሁል ጊዜ በሆነው ባልሆነው ትቆጣለህ? ይህ ከሆነ በአንተ ውስጥ ክፉ ዲያብሎስ አለ፡፡ በምትሄድባቸውና በምትቆምባቸው ቦታዎች ሁሉ ከአንተ ጋር ሲዖልን ተሸክመሃታል፡፡

(ምንጭ፡- www.oodegr.com በእኛ ቤተ ክርስቲያን ‹ዚአከ ለዚያየ፤ ዚያየ ለዚአከ› ተብሎ ከሚነገረው ምሳሌ ጋር አንድ ቢሆንም ለማስተላለፍ የፈለጉት መልዕክት ግን ስለተለየብኝ ተርጉሜ አቅርቤዋለሁ፡፡)

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
ሰባት ወንዶች እንዲሁም ሦስት ሴቶች ልጆቹን በቅጽበት ሲያጣ ፈጣሪውን ያላማረረ ጻድቁ ኢዮብን እስኪ ለአፍታ እናስበው፡፡ ልጆቻቸውን ያጡ ወይም የሚያጡ ብዙ ወላጆች ልጆቹ ከመሞታቸው በፊት የመጨረሻ ቃላቸውን የመስማት፣ እጆቻቸውን የማሻሸትና ጥልቅ በሆነ ቤተሰባዊ ፍቅር የመሳም፣ ከሞቱም በኋላ እንደ ሥርዓቱ ዓይኖቻቸውን የመክደን እና አስከሬናቸውን አጥቦ የመገነዝ እድል አላቸው። ጻድቁ ኢዮብ ግን ከእነዚህ ውስጥ አንዱን እንኳን አላገኘም። ልጆቹ በታላቅ ወንድማቸው ቤት ሲበሉና ሲጠጡ ድንገት ዐውሎ ነፋስ ተነሥቶ ቤቱን ደርምሶ ስለ ገደላቸው እነርሱን ተንከባክቦ የማስታመም እድል አላገኘም። ነፍሳቸውም በወጣችበት ደቂቃ ዓይኖቻቸውን አልከደነም፡፡

የሞቱት ድንጋይ ተጭኗቸው ስለሆነና አስከሬናቸውን ለማውጣት በሚደረገው ቁፋሮ ወቅት አንዳንዶቹ ሕዋሳቶቻቸው በጣም ስለሚጎዱ ሙሉ አካላቸውን የመቅበሩ ነገር ያጠራጥራል፡፡ ታዲያ እነዚህ ሁሉ መከራዎች በአንድ ጊዜ ቢደራረቡበትም ጻድቁ ኢዮብ ግን ‹‹እግዚአብሔርን አልሰደበም፣ መላእክትን አልረገመም››። ይልቅ ወደ ምድር ሰግዶ ‹‹እግዚአብሔር ሰጠ፣ እግዚአብሔርም ነሣ፤ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን›› ብሎ አምላኩን አመሰገነ። ትንሣኤ ባልተሰበከበት፣ የሰው ተስፋ በቀጨጨበት፣ ሞት ጥላውን ባጠላበት በኦሪት ዘመን የነበረ ኢዮብ እነዚያን ሁሉ ልጆች በአንድ ጊዜ አጥቶ እንዲህ ካመሰገነ፣ ስለ ትንሣኤው የተማርንና "የሙታንን መነሣት ተስፉ እናደርጋለን" ብለን የምንጸልይ፣ የኢዮብን ሩብ ያህል እንኳን መከራ ያልደረሰብን እኛ የሐዲስ ኪዳን ምእመናን ምን ያህል አመስጋኞች ልንሆን በተገባን?

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
https://tttttt.me/Dnabel
https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg